የካናዳ ፍርድ ቤት አሜሪካ ለጥገኝነት 'የማትመች' አገር ናት ሲል በየነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የካናዳ ፌዴራል ፍርድ ቤት፤ ካናዳ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የነበራት የጥገኝነት ስምምነት ከዚህ በኋላ ዋጋ የለውም ሲል በይኗል።
ፍርድ ቤቱ ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው አሜሪካ ስደተኞች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየፈፀመች ስለሆነ ነው ብሏል።
ሦስተኛ የጥገኝነት ሃገር [The Safe Third Country Agreement] የተሰኘው ስምምነት የተፈረመው በአውሮፓውያኑ 2014 ሲሆን ስደተኞች ጥገኝነት በጠየቁበት የመጀመሪያ አገር ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ያዛል።
ነገር ግን የፌዴራል ፍርድ ቤቱ ዳኛ አሜሪካና ካናዳ የገቡት ስምምነት ከዚህ በኋላ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው ብለውታል። አሜሪካ ስደተኞችን ልታስር ትችላለች ሲልም ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል።
ብያኔው ለካናዳውያን የስደተኞች መብት ተሟጋቾች ትልቅ ድል ነው ተብሏል።
ከአሜሪካ ወደ ካናዳ ሊገቡ ሲሉ የተከለከሉ ስደተኞች ጠበቆች አሜሪካ ለስደተኞች 'ደህንነት አስጊ' አገር ናት ሲሉ ይሟገታሉ።
ምንም እንኳ ውሳኔው ይተላለፍ እንጂ ተግራባራዊ የሚሆነው በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ የካናዳ ፓርላማ ከተወያየበትና የአሜሪካ ኮንግረስ ምላሽ ከሰጠበት በኋላ ነው ተብሏል።
ነዲራ ጀማል ሙስጠፋ፤ አሜሪካ በስደት ለመቆየት ከተገደዱ ሰዎች መካከል ናት። አሜሪካ ውስጥ በእስር ያሳለፈችው ጊዜ በጣም የሚረብሽና አእምሯዊ ጫና ያሳደረባት እንደነበር ለፍርድ ቤቱ ተናግራለች።
የአሜሪካና ካናዳ ድንበር ሁለት አገራት የሚጋሩት የዓለማችን ትልቁ ድንበር ነው። ድንበሩ 8 ሺህ 891 ኪሎ ሜትር ስፋት አለው።
ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካንን የመሪነት ቦታ ከያዙ በኋላ 58 ሺህ ገደማ ስደተኞች ከአሜሪካ ወደ ካናዳ አቋርጠው ገብተዋል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት በብይኑ ላይ እስካሁን ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጡም።












