ካናዳ ዕፀ ፋርስን ለመዝናኛነት ህጋዊ አደረገች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከኡራጓይ በመቀጠል ካናዳ ዕፀ ፋርስን ለመዝናኛነት ህጋዊ በማድረግ ሁለተኛዋ ሀገር ሆናለች።
ምንም እንኳን የጤናና የአካባቢ ደህንነት ጥያቄዎች እንደተንጠለጠሉ ቢሆንም ሀገር አቀፉ የዕፀ ፋርስ ገበያ ክፍት ሆኗል።
ህጋዊ ከመደረጉ በፊት ቅድመ ዝግጅቶች የተደረጉ ሲሆን በአዲሱ ህግ ዙሪያም ሆነ በአካባቢ ደህንነት ላይ ግንዛቤን ለመፍጠር ለ 15 ሚሊዮን ቤተሰቦች መልዕክት እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
ነገር ግን አሁንም ያልተመለሱ ጥያቄዎች ያሉ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ዕፀ ፋርስ ተጠቅሞ መንዳትና ፖሊስስ በምን መንገድ ነው የሚቆጣጣረው የሚሉት ይገኙበታል።
የተለያዩ የካናዳ ግዛቶችም ዕፀ ፋርስ ይፈቀዳል በሚል ዝግጅትም ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ግዛቶቹና አስተዳደሮቹ ዕፀ ፋርስ የሚሸጡባቸውንም ቦታዎች የሚወስኑ ይሆናል።
በምስራቃዊ ካናዳ በሚገኘው ግዛትም ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ ዕፀ ፋርስን ለመሸጥ ሱቆቻቸውን ከፍተው ታይተዋል።

ካናዳ ዕፀ ፋርስን ህጋዊ ለምን አደረገች የሚሉ ጥያቄዎች መነሳት የጀመሩ ሲሆን እንደ ዋነኛ ምክንያትም የተሰጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ የገቡትንም ቃል ተከትሎ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የቆየው ዕፀ ፋርስን መጠቀም የሚከለክለው ህግ ተግባራዊ ያልተደረገ ሲሆን ምክንያቱም ካናዳ ከዓለም ከፍተኛ ተጠቃሚዎች አንዷ በመሆኗ ነው።
ጨምረው እንደተናገሩትም ህጋዊ የሆነበትም ምክንያት ህፃናትና ወንጀለኞች ዕፀ ፋርስን የማይጠቀሙበት የህግ ማዕቀፍ ለመፍጠር ነው ብለዋል።
ዕፀ ፋርስም ህጋዊ በመሆኑ ምክንያት ማዕከላዊ መንግሥቱ በአንድ አመት ብቻ 400 ሚሊዮን ዶላር ግብር የመሰብሰብ ዕቅድ አለው።
የተለያዩ አውሮፖ ሃገሮችም ዕፀ ፋርስን ለመድሃኒነትነት ህጋዊ በማድረግም ላይ ናቸው።












