ፊልም ፡ በዚህ ዓመት በሆሊውድ ብዙ ሚሊዮን ዶላሮች የተከፈላቸው ተዋናዩች ታወቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዚህ ዓመት የትኞቹ ተዋናዮች ብዙ ሚሊዮን ዶላሮች ተከፈሏቸው? ብሎ ለሚጠይቅ ዘንድሮ ድዋይን "ዘ ሮክ" ጆሐንሰንን በክፍያ የሚያህለው አልተገኘም አጭሩ መልስ ነው።
የሐብታም የገንዘብ መጠን አደባባይ በማስጣት የሚታወቀው ፎርብስ የአዱኛ ዝርዝር መጽሔት ትናንት እንዳስነበበው ከሆነ ድዋይን ጆሐንሰን በዚህ ዓመት ብቻ 87 ሚሊዮን ተኩል ዶላር አጋብሷል።
ይህም ካለፈው ዓመት ሰኔ እስከ ዘንድሮ ሰኔ መሆኑ ነው፤ በፈረንጆች አቆጣጠር።
ደግሞም የድዋይን ከፍተኛ ተከፋይነት ዘንድሮ ለተከታታይ ሁለተኛ ዓመት መሆኑ አስገራሚ ሆኗል።
የቀድሞው የነጻ ትግል ተወዳዳሪና የአነቃቂ ዲስኩርተኛ ጆሐንሰን ዘ ሮክ በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት የምድራችን ትልቅ ገንዘብ ተከፋይ ተዋናይ ተብሎ መሰየሙ ይታወሳል።
ድዋይን ዘ ሮክ ጆሐንሰን ይህ ክፍያው ኔትፍሊክስ ላይ በቅርብ መታየት ለሚጀምረው "ሬድ ኖቲስ" (Red Notice) ለተሰኘው ፊልም ማስታወቂያና ትወና የተከፈለውን 23 ሚሊዮን ዶላር ተኩል ይጨምራል። በፊልሙ ላይ ድዋይን ራሱ መሪ ሆኖ ይተውንበታል።
ሬድ ኖቲስ በቅርብ በኔትፍሊክስ የሚቀርብ አንድ ኢንተርፖል በጥብቅ በሚፈልገው የዓለማችን የሥዕል ቀበኛ ላይ የሚያጠነጥን 'አክሽን ኮሜዲ' ዘውግ ያለው ፊልም ነው።
ከዚህ ባሻገር የስፖርታዊ እንቅስቃሴ አልባሳት ማምረቻ የሆነውና "ፕሮጀክት ሮክ" የሚል ስም ያለው ድርጅቱ ለድዋይን ዘ-ሮክ ጠቀም ያለ ገንዘብ ያስገኝለታል።
ከድዋይን 'ዘ-ሮክ' ጆሐንሰን ጋር 'በሬድ ኖቲስ' ፊልም ላይ አብሮት የሚሰራው ሌላኛው ተዋናይ ራየን ሬይኖልድ 2ኛው ከፍተኛ ተከፋይ ነው፤ በፎርብስ መጽሔት መረጃ መሰረት።
ራየን ሬይኖርልድ 71 ሚሊዮን ዶላር ተኩል ወደ ኪሱ አስገብቷል በዚህ ዓመት።
ይህ ገንዘብ 'ሬድ ኖቲስ' ላይ ለሚተውንበት የተከፈለውን 20 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ሲክስ አንደርግራው (Six Underground) ለተሰኘው ፊልም ደግሞ ሌላ 20 ሚሊዮን የተከፈለውን ይጨምራል።
ፎርብስ የዓለማችን ሦስተኛው ከባድ ተከፋይ ተዋናይና ፕሮዲዩሰሩ ማርክ ዋልበርግ እንደሆነ አስታውቋል።
58 ሚሊዮን ዶላር በዓመት ገቢ አግኝቷል ማርክ። በአራተኛና በአምስተኛ ደረጃ የተቀመጡት ቤን አፍሌክ እና ቪን ዲዝል ናቸው።
ከዚህ ሌላ የቦሊውዱ ኩማር እስከ 10 ከገቡ ከፍተኛ ተከፋዮች ብቸኛው ሆኗል።
በዚህ ዝርዝር ውስጥ ሚራንዳ፣ ዊል ስሚዝ እና አዳም ሳንድለር ይገኙበታል። ጃኪ ቻንም እስከ 10 ባለው ዝርዝር ቦታ አላጣም።
ፎርብስ የወንድ ተዋናይንን ዝርዝ ነው ለጊዜው ይፋ ያደረገው። በቀጣይ ሴት ተዋንያንን እንዲሁ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
ባለፈው ዓመት በዚህ የከፍተኛ ተከፋዮች ዝርዝር ከሴት ተዋንያን ሁሉ ልቃ የተገኘችው ስካርሌት ጆሐንሰን ነበረች፤ 56 ሚሊዮን ዶላር በማፈስ።
ይህ ገንዘብ መጠን ባለፈው ዓመት ከወንዶች ዝርዝር ሰባተኛ ደረጃን የሚያስቀምጥ ነበር።













