ፊልም፡ ዲዝኒ በመዝናኛው ዓለም ስሙን የተከለውን የ20 ሴንቸሪ ፎክስን ስም ቀየረ

በመዝናኛው ኢንደስትሪ ዝመ ገናና የነበረው 20 ሴንቸሪ ፎክስ ተዘጋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ትዌንቲ ሴንቸሪ ፎክስ የሚባለውና በመዝናኛው ዓለም ስሙን በተመልካቾችና በፊልም ባለሙያዎች ውስጥ የተከለው ኩባንያ ከአሁን በኋላ በይፋ እንደማይኖር ዲዝኒ አስታውቋል።

ዲዝኒ ይህንን ውሳኔውን ያሳወቀው ከቴሌቪዥን ስቱዲዮዎች መካከል አንዱ የሆነውን፤ ትዌንቲ ሴንቸሪ ፎክስ ቴሌቪዥንን (20th Century Fox Television)፣ 20 ቴሌቪዥን (20th Television) በሚል መቀየሩን ባሳወቀበት ወቅት ነው።

ይህ ውሳኔ የመጣው ዲዝኒ ከትዌንቲ ሴንቸሪ ፎክስ የፊልም ብራንድ ላይ ፎክስ የሚለውን ቅጥያ መተዉን በታህሳስ ወር ማስታወቁን ተከትሎ ነው።

የፊልም ስቱዲዮው በሆሊውድ ታሪክ ተወዳጅ ፊልሞችን አበርክቷል። ካበረከታቸው ፊልሞች መካከል "ስታር ዋርስ"፣ "ዘ ሳውንድ ኦፍ ሚዩዚክ"፣ "ዳይ ሃርድ" እና "ሆም አሎን" ይገኙበታል።

ባለፈው ዓመት ከ71 ቢሊየን ዶላር በላይ በማውጣት የፎክስን ንብረቶች የገዛው ዲዝኒ ለረዥም ጊዜ የስቱዲዮ መጠሪያ የነበረውን ወደ ትዌንቲ ሴንቸሪ ስቱዲዮስ ቀይሮታል።

ባለፈው ዓመት ዲዝኒ የሩፐርት መርዶክ ፎክስ ሚዲያ ንብረቶችን 71.3 ቢሊየን ዶላር በመግዛት መጠቅለሉ ይታወሳል።

ዲዝኒ የቲቪ ስቱዲዮዎቹንም ስም የቀየረ ሲሆን አዲስ ስምና ዓርማ ይኖራቸዋል ብለዋል።

ይህም ኤቢሲ ስቱዲዮስ፣ ኤቢሲ ሲግኔቸር ስቱዲዮስ ወደ ኤቢሲ ሲግኔቸር እንዲሁም ፎክስ 21 ቴሌቪዥን ወደ ተችስቶን ቴሌቪዥን ተቀይረዋል።

የዲዝኒ ቴሌቪዥን ስቱዲዮስ ፕሬዝዳንት ክሬግ ሁኔግስ አዲሶቹ የፊልምና የቴሌቪዥን ስቱዲዮዎች የድርጅቱን ነባር ስምና ዝና እንዲሁም የፈጠራ ብቃት እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል።

20 ሴንቸሪ ፎክስ ቴሌቪዥን የተመሰረተው እኤአ በ1949 ሲሆን በርካታ ዝነኛ የቴሌቪዥን ትርዒቶች ወደ ሕዝብ እንዲደርሱ አድርጓል። ከእነዚህም መካከል ዘ ሲምፕሰንስ፣ ማሽ (M*A*S*H ) እንዲሁም ቀዳሚው የባት ማን ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፣ ሞደርን ፋሚሊ ይገኙበታል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ትዌንቲ ሴንቸሪ ስቱዲዮ ዳግም ስሙ ሲቀየር ዲዝኒ ከመርዶክ ስምና ተጽዕኖ ራሱን ለመነጠል እየሞከረ ነው ተብሎ ነበር።

20 ሴንቸሪ ፎክስ ቴሌቪዥን እንደ ሲምፕሰን ላሉ ተከታታይ ድራማዎችን አበርክቷል

የፎቶው ባለመብት, FOX TV

ዲዝኒ በአሜሪካ የመገናኛ ብዙሃን ውስጥ በኤቢሲ ኔትወርክ አማካኝነት ከፍተኛ ስምና ዝና አለው።

አሁን ደግሞ ከኔትፍሊክስ ጋር በመፎካከር የራሱን የፊልም እና ተከታታይ ድራማዎች ለማሰራጨት ዲዝኒ ፕላስ የሚል ከፍቷል (Disney+)።

ትዌንቲ ሴንቸሪ ፎክስ ፊልም ስቱዲዮ እንደ አቫተርና ታይታኒክ ያሉ የምንጊዜም ምርጥ ፊልሞችን ፕሮዲውስ ያደረገ ኩባንያ ነው።

ትዌንቲ ሴንቸሪ ፎክስ የተመሰረተው (እኤአ) በ1935 ቴዌንቲዝ ሴንቸሪ ፒክቸርስና ፎክስ ፊልምስ ሲቀላቀሉ ነው።

ዲዝኒ ፊልሞች በበኩላቸው በፊልም አፍረቃሪያን ልብ ውስጥ መኖር የጀመሩት (እአአ) በ1937 ስኖው ዋይት እና ሰቨን ድዋርፍስ ከሥራ በኋላ ሲሆን አሁን ደግሞ የስታር ዋርስ ተከታታይ ፊልሞችን እንዲሁም ማርቭል ስቱዲዮስ በመያዝ ዝናውን እና ተመራጨነቱን እንዳስጠበቀ ይገኛል።