የአሜሪካ ምርጫ ፡ ጆ ባይደን ካመላ ሐሪስን የምርጫ ውድድር ሸሪካቸው አድርገው መረጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሴናተር ካማላ ሐሪስ የጆ ባይደን ፕሬዝዳንታዊ ፉክክር ሸሪካቸው ሆናለች።
ለዚህ ስትታጭ ሐሪስ በአሜሪካ ምርጫ ታሪክ የመጀመርያዋ ጥቁር እስያዊ አሜሪካዊት ሴት ናት።
ሴናተር ሐሪስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ውስጥ አባል የሆነችው የካሊፎርኒያን ግዛትን ወክላ ነው።
ዘሯ ከጃማይካ እና ከሕንድ ይመዘዛል። ለዚህ ከፍተኛ ቦታ ከታጩ ሴት ፖለቲከኞች አንዷ እንደምትሆን ቅድመ ግምት ነበር።
የቀድሞዋ የካሊፎርኒያ ዐቃቤ ሕግ ሐሪስ በፀረ ዘረኝነት እንቅስቃሴ ውስጥ ድምጽ ስታሰማ ነበር። በተለይም በአሜሪካ ውስጥ የፖሊስ ክንድ በጥቁሮች ላይ መበርታቱን በመቃወም የፖሊስ ማሻሻያ እንዲደረግ ስትቀሰቅስ ትታወቃለች።
ጆ ባይደን በኅዳር 3ቱ የአሜሪካ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕን ይገጥማሉ። ባይደንን በአነጋገርም ሆነ በክርክር ቀዘዝ ማለታቸውን ተከትሎ "እንቅልፋሙ ጆ" እያሉ የሚሸነቁጧቸው ዶናልድ ትራምፕ በመጪው ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚያሸንፉ ከወዲሁ እርግጠኛ ሆነዋል።
ባይደንና ትራምፕ በአንድ ጎን፣ ሐሪስና ፔንስ በሌላ ክርክር ይገጥማሉ።
ሐሪስ ከትራምፕ ምክትል እና ከአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ጋር በጥቅምት 7 ክርክር ያደርጋሉ። ክርክሩም በዩታ ግዛት፣ ሌክ ሲቲ ከተማ ይሆናል።
በአሜሪካ የምርጫ ፖለቲካ ታሪክ እስከዛሬ ለምርጫ አሯሯጭነት ሁለት ሴቶች ብቻ ናቸው ተመርጠው የሚውቁት። በ2008 ሳራ ፔለን እንዲሁም 1984 ገራዲን ፌራሮ ናቸው፤ ሁለቱም አልተሳካላቸውም።
እስከ ዛሬ ሪፐብሊካንም ሆነ ዲሞክራት ፓርቲዎች ከነጭ አሜሪካዊ ውጪ ጥቁርም ሆነች እስያዊት ሴት ለፕሬዝዳንታዊ ፉክክር መርጠው አያውቁም።
ጥቁር ወይም እስያዊት ዝርያ ያላት አሜሪካዊት ፕሬዝዳንትም ኖራ አታውቅም።
የጾታ እኩልነት የመንፈስ አባት ነኝ የምትለው አሜሪካ እስከዛሬ በታሪኳ ሴት ፕሬዝዳንት ኖሯት አለማወቁ ብዙዎችን ግር የሚያሰኝ ነው።
ሂላሪ ክሊንተን በቀድሞው ምርጫ ከፍተኛ የመራጭ ድምጽ "ፖፑላር ቮት" ቢያገኙም ዋይት ሐውስን በቅርብ ርቀት ተመኝተውት ጎራ ሳይሉበት ዕደሉ አምልጧቸዋል።
ካማላ ሐሪስ ማን ናት?
ሐሪስ 55 ዓመቷ ነው። ለዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የዲሞክራቶች እጩ ለመሆን ሩጫ ጀምራ ኋላ ላይ በበቃኝ የወጣች ሴት ናት።
በውድድሩ ወቅት አሁን የምርጫ ሸሪክ ካደረጓት ጆ ባይደን ጋር በተደጋጋሚ ተጋጭተዋል፣ ተከራክረዋል፣ አንድ ሁለት ተባብለዋል።
ሐሪስ የተወለደችው በኦክላንድ፣ ካሊፎርኒያ ነው። አባትና እናቷ ስደተኞች ነበሩ። እናቷ ከሕንድ አባቷ ደግሞ ከጃማይካ ናቸው።
ትምህርቷን የተከታተለችው የጥቁሮች ኮሌጅ በሚባለው ሐዋርድ ዩኒቨርስቲ ነው። በካሊፎርኒያ ግዛት ዐቃቤ ሕግ ሆና ስትሰራ ስኬታማ አሰራሮችን ዘርግታለች ተብላ ትሞካሻለች።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጆ ባይደን ሐሪስን የምርጫ ሸሪክ አድርገው ስለመምረጣቸው አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀው "ባይደን አስቀያሚ ሴት ነው የመረጠው፤ ምን ነካው ባይደን? በምርጫው ተደንቂያለሁ" ብለዋል።













