ሚሼል ኦባማ፡ ቀጣይዋ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት?

ጆ ባይደን እኔ የዲሞክታሪክ ፓርቲ እጩ ውድድርን ካሸነፍኩ የፕሬዝዳንታዊ የውድድር ሸሪኬ ሴት ትሆናለች ብለው በመጋቢት ወር ቃል ገብተው ነበር።
አሁን ቃላቸውን መፈጸም የግድ ነው። ማን ትሆን ለዚህ ትልቅ ኃላፊነት የምትታጨው?
የአሜሪካ ፖለቲካ አዋቂዎች የሚከተሉት ሴቶቹ ሰፊ ዕድል አላቸው ይላሉ።
ካማላ ሀሪስ
ሀሪስ የባይደን የውድድር ሸሪክ ለመሆን ሰፊ ዕድላ አላት።
የካሊፎርኒያ አቃቤ ሕግ ነበረች። በአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ካሊፎርኒያን በመወከል አባል ናት።
በሳንፍራንሲስኮም የአንድ ቀጠና አቃቢ ሕግ ሆና ሠርታለች።
እናቷ ከሕንድ ናቸው፣ አባቷ ከጃማይካ። ባለፈው ዓመት ለፕሬዝዳንትነት መፎካከርም ጀምራ ነበር።
ሃሪስ ለባይደን በቅርቡ 2 ሚሊዮን ዶላር በበይነ መረብ ገንዘብ ማሰባሰብ ችላ ነበር፤ በግዛቷ ካሊፎርኒያ።
ባይደን ሸሪኩ ጥቁር ሴት እንድትሆን ፍላጎት አላቸው። በተለይ በጥቁር አሜሪካዊያን ዘንድ። ይህንንም ፍላጎት በደንብ ታሟላለች።
ከጆርጅ ፍሎይድ ጋር በተያያዘ ደግሞ ሰሞኑን በነበሩ ትላልቅ ሰልፎች የሕዝብ ትኩረት ያገኙ ንግግሮችን አድርጋ ነበር።

ግሪቸንዊትመር
ዊትመር የሚቺጋን ገዥ ከሆነች ገና ሁለት ዓመቷ ነው። እምብዛምም አትታወቅም ነበር። ኮሮናቫይረስ ነው ይበልጥ ያሳወቃት ይባላል።
ቫይረሱን በሚቺጋን ለመቆጣጠር በወሰደችው እርምጃ ዶናልድ ትራምፕ አፍ ውስጥ ገባች። በአሜሪካዊያን ዘንድ ይበልጥ ያስተዋወቃትም በትራምፕ አፍ ውስጥ መግባቷ ሳይሆን አይቀርም።
ከዓመታት በፊት በ2016 ሂላሪ ክሊንተን በሚቺጋን በዶናልድ ትራምፕ የተበለጡት ለጥቂት ጊዜ ነበር።
ያን ጊዜ በሚቺጋን ሂላሪ አሸንፈው ቢሆን ኖሮ ትራምፕ ፕሬዝዳንት ላይሆኑ ይችሉ ነበር።
ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ባይደን እንዳይገጥማቸው ዊትመርን የውድድር ሸሪካቸው ሊያደርጓት ይገባል የሚሉ ተንታኞች አሉ።

ታሚ ደክዎርዝ
ታሚ ደክዎርዝ የኢሊኖይ ሴናተር ናት። በኢራቅ እርሷ ታበረው የነበረው ሄሊኮፕተር በጠላት ተመትቶ በመውደቁ ነው ሁለት እግሮቿን ያጣችው። ከዚያ በኋላም ከወታደር ቤት አልወጣችም። ጡረታ የወጣችው የሌተናል ኮሎኔልነት ማዕረግ ይዛ ነው።
ከዚያ በኋላ በዶናልድ ትራምፕ ዘመን የጡረታ ጉዳዮች ረዳት ዋና ጸሐፊ ሆና አገልግላለች።
ደክዎርዝ በታችኛው ምክርት ቤት እንደራሴ ሆና ካገለገለች በኋላ በ2016 የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ወንበርን አሸንፋለች።
የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ለመግባት የመጀመርያዋ የታይላንድ ዝርያ ያላት ሴት ናት።
በአሜሪካ ታሪክ ሁለት እግሯን በአደጋ አጥታ የኮንግረስ አባል የሆነች የመጀመርያዋ ሴት ናት።
በ2018 የሴኔት አባል ሆና እያገለገለች ልጅ የተገላገለች የመጀመርያዋ ሴት ናት፣ ደክዎርዝ።
እርግጥ ነው ኢሊኖይ ግዛት የዲሞክራቶች ናት። ሆኖም በብዙ መልኩ ባይደን ታሚ ደክዎርዝን ሸሪካቸው አድርገው ሊመርጧት የሚችሉበት ዕድል አለ።

ኤልዛቤት ዋረን
ኤልዛቤት ዋረን በቅድመ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ብዙ ርቀት ትሄዳለች፣ ዲሞክራቶችን ትወክላለች ተብላ ስትጠበቅ በአጭር ቀረች።
በ2019 አጋማሽ ጥሩ ተጉዛ በሕዝብ ድምጽ መለኪያ ሁሉ መምራት ጀምራ ነበር። ከዚያ ድንገት ደጋፊዎቿ እንደ ጉም ተነኑ። ግማሾቹ ወደ በርኒ ሳንደርስ ሄዱ።
ብዙዎች እርሷ ውድድሩን ጥላ ስትወጣ ሳንደርስን ይቅናዎ ብላ ትባርካቸዋለች፤ ደጋፊዎቿንም ወደ ሳንደርስ ትሸኛቸዋለች ብለው ጠብቀው ነበር። ይህን ባለማድረጓ ባይደን ውስጥ ውስጡን ሳያደንቋት አልቀሩም።
ባይደን ኤልዛቤት ዋረንን በዚህም ሆነ ባላት እምቅ አቅምና ድጋፍ የምርጫ ሸሪካቸው ሊያደርጓት ሰፊ ዕድል አለ ይላሉ ተንታኞች።

ታሚ ባልድዊን
ከአራት ዓመት በፊት ሂላሪ ክሊንተርን በዊስኮሲን ቅስቀሳ አለማድረጋቸው ቅሬታን ፈጥሮ ነበር፡፡ ግዛቷን ንቀዋት ይሆን? ዋጋ አስከፈለቻቸው። ዲሞክራቶች ይህንን ስህተት ይደግማሉ ተብሎ አይጠበቅም።
ባይደን ዊስኮንሲንን መዘንጋት ካልፈለጉ ታሚ ባልደዊንን ሸሪካቸው አድርገው ሊመርጧት ይችላሉ።
ታሚ በሴኔት ውስጥ 2ኛ ዓመቷ ነው። በሕግ መምሪያ ታችኛው ምክር ቤት ለ14 ዓመታት አገልግላለች።
እሷ ብትመረጥ አንድ አዲስ ታሪክም ይመዘገባል።
በግልጽ የተመሳሳይ ጾታ ወዳጅ የሆነች ሴት ለእጩ ፕሬዝዳንትነት ውድድር ምክትል ሆኖ መወዳደር አዲስ ታሪክ ነው። ለሕግ መወሰኛ ምክር ቤትም ቢሆን በአሜሪካ ታሪክ ግልጽ የተመሳሳይ ጾታ ወዳጅ የሆነች ሴት አባል ሆና አታውቅም።

ክሪስተን ሲኒማ
በ2018 ከሪስተን ሲኒማ አሪዞናን ለማሸነፍ በ30 ዓመት የመጀመርያዋ ሴት ናት።
ሲኒማ ወጣት ናት፣ ቆንጆ ናት። የቴሌቪዥን ተመልካቾችን የመማረክ አቅም አላት። በፖለቲካ አቋሟም አማካይ አመለካከት ትይዛለች ይሏታል።
ድንገቴ ባህሪ አላት፣ አትፈራም፣. ያልተጠበቁ ነገሮች በማድረግ ትታወቃለች። የሚዲያ ትኩረትን በቀላሉ መሳብ ትችላለች።
በቅርቡ ሐምራዊ አርቴፊሻል ጸጉር አድርጋ በሴኔት መታየቷ ሲያነጋግር ነበር። ያደረገችው ዊግ ርካሽ የ12 ዶላር ተራ ዊግ ነበር። ጸጉር ቤት አትሂዱ በኮሮናቫይረስ ዘመን ዝም ብላችሁ ዊጋችሁን አጥልቁ የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነበር የሞከረችው ተብሏል።
ዶናልድ ትራምፕ ባይደንን በሹፈት "እንቅልፋሙ ባይደን" እያሉ ነው የሚጠሩት። ጆ ባይደን እንቅልፋም ባይባሉም ትንሽ ፍዝ ባህሪ ነው ያላቸው። ክሪስተን ሲኒማ ንቅት፣ ፍክት ያለችና ጉዳይ መቀስቀስ የምትችል ስለሆነች የባይደንን ፍዝነት ታካክስላቸው ይሆናል።

ቫል ደሚንግስ
ባለፈው ዓመት ቫል ደሚንግስ እምብዛምም የማትታወቅ የኮንግረስ አባል ነበረች።
ከዚያ ድንገት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፒሎሲ የትራምፕ ክስ የሚያየው ኮሚቴ ሊቀ መንበር አደረገቻት። ከዚያ ሁሉም አወቃት።
ቫል ደሚንግስ ገና ጆርጅ ባይደን በግፍ በነጭ ፖሊስ ከመገደሉ በፊት ጉዳዩን የአሜሪካዊያን ጉዳይ ለማድረግ ጥራለች።
የቀድመው የኦርላንዶ፣ ፍሎሪዳ የፖሊስ አዛዥ ቫል በባይደን ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ጥቁር ሴት ሸሪኮች አንዷ ናት።
አንጻራዊ በሆነ መልኩ ከሌሎች አነስ ያለ የፖለቲካ ጥበብ ያላት ቫል ባይደን የጥቁሮችን ጉዳይ መሪ ጉዳዬ ላድርገው ካሉ ይቺ ሴት ወሳኝ ልትሆነን ትችላለች።

ሚሼል ግሪሻም
በቀዳሚው የምርጫ ፍክክር ወቅት የስፓኒሽ ዝርያ ያላቸው አሜሪካዊያን ለባይደን ድምጻቸውን ለመስጠት አቅማምተዋል።
በካሊፎርኒያ፣ በቴክሳስና በኔቫዳ በርኒ ሳንደርስ ባይደንን በልጠዋቸው ነበር። አንዱ ምክያትም ይኸው ሊሆን ይችላል።
ባይደን የድጋፍ መሰረታቸው የስፓኒሽ ዝርያ ባላቸው አሜሪካዊያን ዘንድ ከፍ እንዲል ከፈለጉ የኒው ሜክሲኮ ገዥ ሚሼል ግሪሻም ወሳኝ እጩ ሆነው ይታያሉ።

ስታንሲ አብራምስ
ስታንሲ የተለመደ ጮሌ ፖለቲከኛ የሚፈለግበት ዓይነት የሥራ ታሪክና ተሞክሮ የላትም።
ጆርጂያን ወክላ በሕግ መምሪያ ምክር ቤት ውስጥ ለ10 ዓመት ቆይታለች። በ2018 የጆርጂያ ገዢ ለመሆን ተወዳድራ ለጥቂት ተሸንፋለች።
ከሌሎች እጩዎች በተለየ አብራምስ የባይደን ምክትል ለመሆን ብዙ ርቀት ሄዳለች። 'ሸሪክህ ልሁን' ብላ በግልጽ ጠይቃለች።
ብዙዉን ጊዜ እጩ አድርገኝ ብሎ በግልጽ መቀስቀስ የተለመደ አይደለም። በዲሞክራቲክ ፓርቲ ውስጥ አብራምስ አዲስ ድምጽ ሆናለች ይላሉ ተንታኞች።

ኬይሻ ቦተምስ
ጆርጅ ፍሎይድ በነጭ ፖሊስ መገደሉን ተከትሎ የተነሳው አመጽ ለትልልቅ ከተሞች ከንቲባዎች የመታያ መድረክ ከፍቶላቸዋል።
የአትላንታ ከንቲባ ኬይሻ በዚህ ረገድ ትጠቀሳለች።
ፖሊስ ተመጣጣኝ እርምጃ ብቻ እንዲወስድ በማግባባትም፣ ሰልፈኞቹና ጥያቄዎቻቸው የእርሳቸውም ጥያቄ እንደሆነ በማንሳትም ድምጿን ከፍ አድርጋ ጉዳያችሁ ጉዳዬ ነው ብላለች።
እርሷ ራሱ ጥቁር መሆኗና የርሷም አራት ልጆች እጣ ፈንታ እንደሚያሳስባት ተናግራ ነበር።
ኬይሻ "የ12 ዓመት ልጄን እባክህን በአሻንጉሊት ሽጉጥ አትጫወት እለዋለሁ፤ ምክንያቱም ፖሊስ የምር ሽጉጥ የያዝክ መስሎት እንዳይተኩስብህ" ስል እመክረዋለሁ ብላ መናገሯ የብዙዎችን ስሜት የነካ ጉዳይ ነው።
በከንቲባነት ገና የጀመሪያ ዘመኗን እያገባደደች ቢሆንም ኬይሻ የባይደን ተቀዳሚ ምርጫ ልትሆን እንደምትችል ይገመታል።

ሱሳን ራይስ
የሱዛን ራይስ በዚህ ዝርዝር ውስጥ መካተት ለብዙዎች አዲስ ዜና ነው። ምክንያቱም ምንም የመመረጥም ሆነ የቅስቀሳ ልምድ የላትም። ብዙ አሜሪካዊያንም ያውቋታል ማለት ይከብዳል።
ይቺ ዲፕሎማት ግን ባይደን ጠንቅቀው ያውቋታል። ምክንያቱም በኦባማ ጊዜ በዋይት ሐውስ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሆና ሰርታለች። በኋላም በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደርም ሆና አገልግላለች።
ራይስ የባይደን ምርጫ ከሆነች በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ የነቃ ሚና ይኖራታል ተብሎ ይገመታል።
ራይስን ሪፐብሊካኖች አይወዷትም። በ2012 በሊቢያ ቤንጋዚ የአሜሪካ አምባሳዳር መገደልን ተከትሎ የአሜሪካንን ሕዝብ ዋሽታለች ይሏታል።

ሚሼል ኦባማ
የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ለዚህ ቦታ ከበቂ በላይ መሆኗ ነው ችግሩ። እጅግ ተወዳጅ ሴት ናት ሚሼል፤ በአሜሪካዊያን ዘንድ።
ፈተናው የሚሆነው ይኸው ነው።
አንደኛ እርሷ ፖለቲካ ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌላት "ቢካሚንግ" በሚለው የግለታሪክ መጽሐፏ ገልጻለች።
ሁለተኛው ፈተና እርሷ የባይደን ሽርክ ብትሆን ባይደንን ዞር ብሎ የሚያይ አይኖር ይሆናል።
ትኩረቱ ሁሉ እርሷ ላይ ይሆንና ሌላ ጉዳት ያመጣል።
በተለምዶ ምክትል የሚሆነው ሰው እንደ ኮከብ እንጂ እንደ ጨረቃ እንዲደምቅ አይፈለግም። ሚሸል ኦባማ ግን ጨረቃ ናት።













