የቤይሩት ነዋሪዎች ለደረሰው ፍንዳታ መንግሥት ተጠያቂ ነው እያሉ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቤይሩት ነዋሪዎች ማክሰኞ እለት የደረሰው ከባድ ፍንዳታ በቸልተኝነት ምከንያት የተፈጠረ ነው በማለት ቁጣቸውን መንግሥት ላይ እየገለፁ ነው።
ፕሬዝደንት ማይክል አውን ፍንዳታው ባገጠመበት ቦታ ላይ 2750 ቶን የሚመዝን አልሙኒየም ናይትሬት ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ለስድስት ዓመታት ተከማችቶ ነበር ማለታቸው ይታወሳል።
በርካቶች ባለስልጣናትን በሙስና፣ በቸልተኛነትና ሃብት በማባከን ይከሷቸዋል።
በሊባኖሷ መዲና ቤይሩት በተከሰተው ከባድ ፍንዳታ ቢያንስ 135 ሰዎች መሞታቸውን እና ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት እንደደረሰባቸው ተነግሯል።
ለሁለት ሳምንት ያህል የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ተደንግጓል።
የፀጥታ ኃይሎች ፍንዳታው የደረሰበትን ስፍራ አጥረው የነፍስ አድን ሰራተኞች በፍርስራሽ ውስጥ ተቀብረው ያሉ አስከሬኖችን እየፈለጉ ነው። አሁንም በርካቶች መጥፋታቸው እየተነገረ ነው።
የህብረተሰብ ጤና ሚኒስትሩ ሃማድ ሃሰን በፍንዳታው የተጎዱ እና የህክምና ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎችን ለማከም የሊባኖስ ሆስፒታሎች የአልጋ እና ህክምና ቁሳቁስ እጥረት ገልፀዋል።
"ቤይሩት እያለቀሰች፣ ቤይሩት እየጮኸች ነው፤ ሰዎች ተጨንቀዋል፤ ዝለዋል" በማለት ዜጎች ፍትህን በመጋፈጥ ኃላፊነት እንዲወስዱ ለቢቢሲ የተናገረው የፊልም ባለሙያው ጁድ ቼሃብ ነው።
በሆስፒታል የሚገኘው የቤይሩት ነዋሪ የሆነው ቻዳይ ኤልሜኦውቺ ናውን ደግሞ "ብቃት በሌላቸው ሰዎች፣ ብቃት በሌለው መንግሥት እየተመራን እንደሆነ ሁሌም አውቅ ነበር።. . . ነገር ግን አንድ ነገር ልንገራችሁ - አሁን የሰሩት ነገር ሙሉ በሙሉ ወንጀል ነው" ብሏል።
ረቡዕ ዕለት መንግሥት የቤይሩት ወደብ ባለስልጣናት ከፍንዳታው ጋር በተያያዘ ምርመራ በመጀመሩ በቁም እስር ውስጥ መሆናቸውን ተናግሯል።
የሌባኖስ የጦር ኃላፊ ለፍንዳታው ተጠያቂ ሆነው የሚገኙት ላይ የሚቻለውን “ከፍተኛ ቅጣት ይተላለፍባቸዋል” ብለዋል።
ፍንዳታው ያጋጠመው የከተማዋ ወደብ የሚገኝበት አቅራቢያ ሲሆን በስፍራው ተከማችቶ የነበረው አልሙኒያም ናይትሬት ከ6 ዓመታት በፊት ከአንድ መርከብ ላይ ወርዶ በስፍራው እንዲከማች ተደርጓል።
ይህ ፍንዳታ የተከሰተው የሊባኖስ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት ነው።
የዓለም ምጣኔ ሃብት ፎረም በዓለማችን ላይ በከፍተኛ ውዝፍ እዳ ውስጥ ከሚገኙ አገራት መካከል ሊባኖስን በሦስተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል።
ከሳምንታት በፊት ሥራ አጥ የሆኑ የሊባኖስ ወጣቶች አደባባይ ወጥተው ነበር። የቫይረሱን ስርጭትም የአገሪቱን ኢኮኖሚ 'ከድጥ ወደ ማጡ' እንዲገባ ሊያደርገው እንደሚችል ተገምቷል።
ከዚህም በተጨማሪ በአውሮፓውያኑ 2005 ላይ የቀድሞ የሌባኖስ ጠቅላይ ሚንስትር ራፊክ ሃሪሪን ገድለዋል የተባሉ አራት ተጠርጣሪዎች ላይ የፊታችን ዓርብ በሌሉበት ብይን ይሰጣል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ነው ፍንዳታው ያጋጠመው።
በጠቅላይ ሚንስትሩ ግድያ የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው አራቱም ግለሰቦች በኢራን መንግሥት የሚደገፈው የሔዝቦላህ ቡድን አባላት ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አልሙኒየም ናይትሬት ምንድነው?
አልሙኒየም ናይትሬት በርካታ ጠቀሜታዎች ቢኖሩትም፤ አብዛኛውን ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውለው ለእርሻ ሥራ ማዳበሪያነት እና ተቀጣጠይ ነገር ሆኖ ነው።
አልሙኒየም ናይትሬት ከእሳት ጋር ከተገናኘ እጅግ ተቀጣጣይ ሲሆን እንደመጠኑ ፍንዳታ ያስከትላል።
በእሳት ሲያያዝ ናይትሮጅን ኦክሳይድ እና አሞኒያ ጋዝ የሚባሉ ለጤና ጎጂ የሆኑ አደገኛ የጋዝ ልቀትን ያስከትላል።
ይህ ኬሚካል አደገኛ ተቀጣጣይ እንደመሆኑ መጠን የሚጓጓዝበት እና የሚከማችበት ሁኔታን በተመለከት ጥብቅ መመሪያዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ።
አልሙኒየም ናይትሬቱ ለምን አስፈለገ?
የሌባኖስ ዜጎች እንዴት ከ2700 ቶን በለይ የሚመዝን ተቀጣጣይ ነገር በመሃል ከተማ በመኖሪያ ስፍራ ላይ ይከማቻል ሲሉ እየጠየቁ ይገኛሉ። የአገሪቱ ፕረዝደንት አልሙኒየም ናይትሬቱ ለስድስት ዓመታት በስፍራው ተከማችቶ መቆየቱን ተናግረዋል።
ዜጎች ይህ "የመንግሥት እንዝላልነትን የሚያሳይ ነው" እያሉ አጥብቅ የመንግሥትን ቸልተኝነት እየኮነኑ ይገኛሉ።
የመከከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ የቻተም ሃውስ ፕሮግራም መሪ የሆነችው ሊና ካሃቲብ፤ "2750 ቶን አልሙኒየም ናይትሬት ማን ምን ሊያደርግለት ይፈልጋል?" ስትል ጠይቃለች።
ሊና ይህ ኬሚካል ተቀጣጣይ ነገሮችን ለመሠራት ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል በማስታወስ፤ የሌባኖሱ ታጣቂ ኃይል ሔዝቦላህ የቤይሩት ወደብ በመጠቀም አልሙኒየም ናይትሬት በድብቅ ወደ አገር ውስጥ እንደሚያስገባ ተናግራለች።
ይሁን እንጂ አልሙኒየም ናይትሬቱ ይህን አይነት ጉዳት እንዲያስከትል ያደረገው ምን እንደሆነ አልተረጋገጠም።
የቤይሩት አስተዳዳሪ የሆኑት ማርዋን አባውድ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ፍንዳታው ከ300 ሺህ በላይ ሰዎችን ቤት አልባ አድርጓል።
አስተዳዳሪው ጨምረው እንደተናገሩት በፍንዳታው ምክንያት የደረሰው ጉዳት በገንዘብ ሲለካ ከ3-5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመት ተናግረዋል።
አስተዳዳሪው" ቤሩት የምግብ የአልባሳትና ቤቶችን መልሶ ለመገንባት የሚኣገለግሉ ቁሳቁሶች ድጋፍ ትፈልጋለች" ቤሩት ለስደተኞች መቆያ ትፈልጋለች" ብለዋል።
በርካታ አገራት ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል። ሶስት የፈረንሳይ አውሮፕላኖች 55 የነፍስ አድን ሰራተኞችን፣ 500 ሰዎችን ማከም የሚያስችል የህክምና ቁሳቁሶችን፣ እና ተንቀሳቃሽ ክሊኒክ ጭነው እንደሚመጡ ፕሬዝዳንት ማክሮን ተናግረዋል።
የአውሮፓ ህብረት፣ ሩሲያ፣ ቱንዚያ፣ቱርክ፣ኢራን እና ከወታር እርዳታ የላኩ ሲሆን ዩናእትድ ኪንግደምምም የሕክምና ባለሙያዎችን እና የሰብዓዊ ርዳታ ለመላክ ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች።
















