ኢራን በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች ቁጥርን ማሳነሷን አንድ ሾልኮ የወጣ መረጃ አጋለጠ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በኢራን በኮሮናቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር መንግሥት በይፋ ከገለጸው በሶስት እጥፋ እንደሚበልጥ የቢቢሲ ፐርሺያ ምርመራ አረጋገጠ።
ለህዝብ ይፋ ያልሆነ የኢራን መንግሥት አሃዝ የሚያሳየው በኮቪድ-19 ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ወደ 42ሺህ የሚጠጋ ነው። ይሁን እንጂ የአገሪቱ ጤና ሚንስቴር እስካሁን በቫይረሱ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 14ሺህ 405 ነው ይላል።
ይህም ብቻ ሳይሆን ከኢራን መንግሥት የተገኘው መረጃ በቫይረሱ ስለመያዛቸው በይፋ የተነገረው ቁጥር በግማሽ እንዲቀንስ መደረጉን አመልክቷል።
ጤና ሚንስቴር እስካሁን በቫይረሱ ተይዘዋል ያላቸው ሰዎች ቁጥር 278 ሺህ 827 ነው። ይሁን እንጂ የአገሪቱ መንግሥት 451ሺህ 024 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አረጋግጧል።
የኢራን መንግሥት በቫይረሱ የተያዙ እና የሞቱ ሰዎች ቁጥርን ከማሳነሱም በተጨማሪ በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታ ማለፍ ከጀመረ ከአንድ ወር በኋላ ነበር የአገሪቱ የጤና ሚንስቴር በቫይረሱ ሳቢያ የሰው ህይወት ማለፉን ሪፖርት ያደረገው።
ይህ መረጃ እንዳረጋገጠው፤ መንግሥት የመጀመሪያውን ሟች ይፋ በሚያደርግበት ወቅት 52 ሰዎች ቀድመው በኮቪድ-19 ምክንያት ህይወታቸው አልፏል።
ማንነቱ ይፋ ያልሆነው ምንጭ ለቢቢሲ የላከው መረጃ በመላው ኢራን በየዕለቱ በኮቪድ-19 ተይዘው ወደ ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎችን ዝርዝር መረጃ የያዘ ነበር።
ሥም፣ እድሜ፣ ጾታ፣ ታማሚው የሚታይበት ምልክት፣ ቀን እና ተጠቂው የተጓዳኝ በሽታ ታማሚ ስለመሆኑ እና ሌሎች መረጃዎች ተካተውበታል።
መረጃውን ለቢቢሲ የላከው ምንጭ “እውነቱ መታወቅ ስላለበት” እና “በወረርሽኙ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት የሚደረገው ጥረት መቆም አለበት” በሚሉ ምክንያቶች መረጃውን ለቢቢሲ ለማጋራት መወሰኑ ተመልክቷል።
ለቢቢሲ ቃላቸውን የሰጡ የኢራን የጤና ባለሙያዎች እንዳሉት የአገሪቱ ጤና ሚንስቴር በኢራን መንግሥት የደህንነት አገልግሎት ጫና ይደረግበታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢራን መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት መደበቅ ለምን አስፈለገው?
የቫይረሱ ስርጭት የተቀሰቀበት ወቅት የኢራኑ ኢስላሚክ አብዮት ጥበቃ ዘብ ክብረ በዓል ከሚከመርበት ወቅት ጋር ተጋጭቷል።
ይህም ብቻ ሳይሆን የፓርላሜንታዊ ምርጫን ለማካሄድ ኢራን ደፋ ቀና የምትልበት ወቅት ነበር።
ኢስላሚክ አብዮት ጥበቃ ዘብ ድጋፉን የሚያጠናክርበት ምርጫውም ስኬታማ የሚሆንብት እድል ሰፊ እንደሆነ በመገመቱ አጋጣሚውን በወረርሽኙ ሳቢያ አሳልፎ መስጠት አልተፈለገም ተብሏል።












