ቢሊየነሩ ፒራሚዶችን የገነቡት 'ኤሊየኖች ናቸው' ማለቱ ግብፅን አስቆጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ግብፅ፤ ቢሊየነሩ ኢላን ማስክ ታዋቂ ፒራሚዶቿ በግዑዛን [ኤሊየኖች] ሳይሆን በሰው መገንባታቸውን እንዲያረጋግጥ ጋብዛለች።
ስፔስኤክስ የተሰኘው ኩባንያ ባለቤት የሆነው ማስክ የሴራ ትንታኔ መሰረት ያለው አንድ መስመር በትዊተር ገፁ ላይ ማስፈሩን ተከትሎ ነው ግብፅ ይህን ያለችው።
ሰውዬው የፃፈው ፅሑፍ 'ፒራሚዶችን የገነቡት ኤሊየኖች መሆናቸው የማይካድ ነው' ይላል።
የግብፅ የዓለም አቀፍ ትብብሮች ሚኒስትር ግን ይህ በፍፁም ሃሰት ነው ብለው። ሚኒስትሯ፤ ፒራሚዶቹን የሰሩት ሰዎች ቅሪተ-አካልን መጎብኘት በቂ ማስረጃ ነው ብለዋል።
ተመራማሪዎች፤ በ1990ዎቹ ፒራሚድ ውስጥ የተገኙት መካነ-መቃብራት ጥንታዊው ሕንፃ በግብፃውያን ለመገንባቱ ምስክር ነው ይላሉ።
ጉምቱው የቴክኖሎጂ ሰው ኢላን ማስክ 'ፒራሚድን የገነቡት ግኡዛን ናቸው' ሲል የለጠፈው ሐሳብ ቢያንስ 84 ሺህ ሰዎች ተጋርተውታል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
የዓለም አቀፍ ትብብሮች ሚኒስትሯ ራኒያ አል-ማሻት በትዊተር ገፃቸው የማስክ ተከታይና አድናቂ መሆናቸውን ጠቅሰው ነገር ግን ሰውዬው ፒራሚዶች የተገነቡት በግብፃውያን ፈርዖኖች መሆኑን የሚያሳይ መረጃ መርምሮ እንዲያነብ አሳስበዋል።
ግብፃዊው አርኪዮሎጂስት [የቅድመ-ታሪክ ተመራማሪ] ዛሂ ሃዋስ ለማስክ ምላሽ እንዲሆን አንድ ምስል በአረብኛ ቋንቋ ለጥፏል። ምስሉ፤ የማስክ ሐሳብ 'ፍፁም የማይታመን' ሲል ያጣጥላል።
አርኪዮሎጂስቱ "እኔ የገንቢዎቹን ቅሪት አይቻለሁ። ሰዎቹ ግብፃውያን ናቸው፤ ደግሞም ባሪያዎች አይደሉም" ብሏል ሲል ኢጂፕትቱዴይ ዘግቧል።
ማስክ ግብፃውያንን ካስቆጣው መልዕክቱ በኋላ የቢቢሲ ታሪክ ዘገባን ዋቢ አድርጎ 'ይህ የቢቢሲ ዘገባ እንዴት እንደተሰራ ስሜት የሚሰጥ ትንታኔ ይዟል' ሲል ፅፏል።
ግብፅ ከመቶ በላይ ፒራሚዶች ይኑሯት እንጂ በጣም ታዋቂዎው ታላቁ የጊዛ ፒራሚድ ሲሆን ቁመቱም 137 ሜትር ነው።
ፒራሚዶች ለያኔው የግብፅ ንጉሳውያን ቤተሰቦች መካነ-መቃብር እንዲሆኑ ተደርገው መገንባታቸውን ታሪክ ይዘክራል።
ቢሊየነሩ ኢላን ማስክ ብዙ ጊዜ መሰል አወዛጋቢ አስተቶችን በመስጠት ይታወቃል።












