በአፍጋኒስታን መኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ ቢያንስ 17 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በአፍጋኒስታን ሎጋር ግዛት በመኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ ቢያንስ 17 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ።
ፍንዳታው ከባድ እንደነበር ተገልጿል። የቦምብ ፍንዳታው የደረሰው ታሊባን የኢድ በዓልን ለማክበር የተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ ነው።
ታሊባን በጥቃቱ እጄ የለበትም በማለት የተናገረ ሲሆን፣ እስካሁን አይኤስ የተባለው ቡድን ግን ያለው ነገር የለም።
ጥቃቱ በአጥፍቶ ጠፊ የተፈፀመ ሊሆን እንደሚችል የሎጋር ግዛት አስተዳዳሪ ቃል አቀባይ፣ ዴዳር ላዋንግ፣ ለፈረንሳዩ ዜና ወኪል ተናግረዋል።
ፍንዳታው የደረሰው ከግዛቱ አስተዳዳሪ ቢሮ አቅራብያ ሲሆን በርካታ ሰዎች ለኢድ በዓል ሸመታ ላይ እንደነበሩ ተገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
" አሸባሪዎቹ በድጋሜ ጥቃት አድርሰው በኢድ አል አድሃ ምሽት ዜጎቻችንን ገድለዋል" ያሉት የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ታሪቅ አርያን ናቸው።
የታሊባን ቃል አቀባይ፣ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ፣ በበኩላቸው ጥቃቱ "ከቡድኑ ጋር አይያያዝም" ሲሉ ተናግረዋል።
ታሊባንና የአፍጋኒስታን መንግሥት ከአርብ ጀምሮ የሚቆይ የሦስት ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገዋል።
በሁለቱ መካከል የሰላም ስምምነት ይደረሳል የሚል ተስፋ ቢኖርም ድርድሩ በእስረኛ ልውውጥ ምክንያት ዘግይቷል። መንግሥት ታሊባን በቁጥጥሩ ስር ያዋሉትን 1000 የአፍጋን ደህንነት ሰራተኞች ከለቀቀ 5000 የታሊባን እስረኞችን ለመልቀቅ ተስማምቷል።
እስካሁን ድረስ የአፍጋን መንግሥት 4,400 የታሊባን አማፂያን እስረኞችን የለቀቀ ሲሆን፣ የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ በበኩላቸው በአጠቃላይ 1,005 የመንግሥት ደህንነት ሰራተኞች መልቀቃቸውን ተናግረዋል።












