በምሥራቅ ሸዋ ዞን በአንድ ቤተክርስትያን ውስጥ ሰባት ወጣቶች ሞተው ተገኙ

በምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ወረዳ ዮሐንስ ዲዲብሳ በሚባል ቤተክርስቲያን ቅዳሜ ማታ ሰባት ወጣቶች ሞተው መገኘታቸውን የአዳማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ተስፋዬ ኢታና ለቢቢሲ ገለፁ።
ኮማንደር ተስፋዬ ህይወታቸው ካለፉት ሰባት ወጣቶች መካከል ስድስቱ ሴቶች ሲሆኑ አንዱ ወንድ መሆኑን አስታውቀዋል።
እነዚህ ወጣቶች የቤተክርስትያኒቱ መዘምራን ሲሆኑ የፋሲካ ዋዜማን ለማክበር የሄዱ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
ኮማንደር ተስፋዬ ለቢቢሲ እንደገለጹት መዘምራኖቹ የቤተክርስትያኒቷ አገልጋይ በመሆናቸው ምሽት ስምንት ሰዓት ላይ በአንድ አነስተና ክፍል ውስጥ ተኝተው ነበር ይላሉ።
ለፖሊስ በደረሰው ጥቆማ መሰረት 9 ሰዓት በስፍራው መድረሳቸውን የሚናገሩት አዛዡ፤ ስድስቱ ሴቶች ህይወታቸው አልፎ ማግኘታቸውን አንድ ወንድ ደግሞ ሐኪም ቤት ከደረሰ በኋላ ሕይወቱ ማለፉን ተናግረዋል።
የሞታቸውን ምክንያት ለማወቅም የሟቾቹ አስከሬን ለተጨማሪ ምርመራ ወደ አዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል መላኩን የገለጹት ኮማንደር ተስፋዬ፤ ወጣቶቹ የተኙበት ክፍል ጄኔሬተር የሚቀመጥበት ሲሆን በዝናብ ምክንያት ክፍሉን ዘግተውት እንደነበር ገልፀዋል።
ወጣቶቹ ሁሉም የአካባቢው ነዋሪዎች ሲሆኑ በአካባቢው ከወንጀል ጋር የተያያዘ ችግር እንደሌለ የፖሊስ አዛዡ ተናግረዋል።
ፖሊስ በስፍራው በደረሰበ ሰዓት 11 በቤተክርስትያኒቱ የነበሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኮማንደር ተስፋዬ ገልፀዋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽንን መስፋፋት ለመግታት በቤተእምነቶች መሰብሰብ መከልከሉ ይታወሳል።















