ኮሮናቫይረስ: የአፍጋኒስታን ቤተመንግሥት ሠራተኞች በኮቪድ-19 ተይዘዋል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአፍጋኒስታን ፕሬዝዳንት ቤተ መንግሥት የሚሰሩ በርካታ ሠራተኞች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተነገረ።
በቅድሚያ 20 ሠራተኞች በኮቪድ-19 መያዛቸው ቢነገርም እሁድ እለት ኒውዮርክ ታይምስ ባወጣው ዘገባ ግን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 40 ይደርሳል ተብሏል።
የአፍጋኒስታን መንግሥት በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት የተቆጠበ ሲሆን ፕሬዝዳንት አሽራፍ ጋሃኒ እስካሁን ስለመያዝ አለመያዛቸው የታወቀ ነገር የለም።
የ70 ዓመቱ አዛውንት ጋሃኒ እአአ በ1990ዎቹ በካንሰር ምክንያት ቀዶ ጥገና ማድረጋቸው ይታወሳል።
ቅዳሜ እለት አንድ የመንግሥት ባለስልጣን ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል "በፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት ውስጥ የሚሰሩ 20 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። ነገር ግን መደናገጥ እንዳይፈጠር በሚል ተሸፋፍኖ ቀርቷል" ብለዋል።
ሐሙስ ዕለት በትዊተር ላይ የተለቀቀው ምስል ፕሬዝዳንት አሽራፍ ከካቢኔ ሚኒስትሮቻቸው ጋር በቪዲዮ ኮንፍረንስ ስብሰባቸውን ሲያካሄዱ ያሳያል። ነገር ግን በዚያው እለት ፕሬዝዳንቱ የኢራን ባለሰልጣናትን በአካል አግኝተው ሲያናግሩ በሰሌዳው ላይ ተለጥፏል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ

በአፍጋኒስታን እስካሁን ድረስ 933 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሲያዙ 33 ሰዎቹ መሞታቸው ተመዝግቧል።
የአፍጋኒስታን የጤና ሥርዓት ለዓመታት በዘለቀው ግጭትና ጦርነት ምክንያት የተጎዳ ሲሆን አገሪቱ ካላት አነስተኛ የመመርመር አቅም አንጻር ቁጥሩ አነስተኛ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም 150 ሺህ አፍጋናውያን በቫይረሱ ክፉኛ ከተጠቃችው ኢራን ባለፈው ወር ወደ አገራቸው መምጣታቸውን በማንሳት እንዲሁም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከፓኪስታን መመለሳቸውን ተከትሎ የቫይረሱ ስርጭት እንዳይስፋፋ ተሰግቷል።













