ደራሲ ጄ ኬ ሮሊንግ የልጅነት ቤቷን በ17 ሚሊዮን ብር ገዛች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዝነኞቹ ሃሪፖተር ተከታታይ መጻሕፍትና ፊልሞች ደራሲ ጄ ኬ ሮውሊንግ ለማንም ሳትናገር በልጅነቷ ያደገችበትን ቤት በምስጢር እንደገዛችው ተሰምቷል።
በደቡብ ምዕራብ እንግሊዝ በግሎስተሸር ወረዳ በተቴሼል ቀበሌ የሚገኘው ይህ መኖርያ ቤት ደራሲዋ ከ8 ዓመት እስከ 18 ዓመቷ ድረስ የኖረችበት ባለ አንድ ወለል መኖርያ ቤት ነው።
ግሎስተሸር ግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርበትና ከለንደን በ151 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ስፍራ ነው።
በግሎስተሸር አካባቢ በተቴሼል ቀዬ የሚገኘው ይህ ቸርች ኮቴጅ መኖርያ ቤት በአርክቴክት ሄንሪ ዉድየር በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የተገነባ ታሪካዊ ቤት እንደሆነ ይታመናል።
የእንግሊዝ መንግሥት ለዚህ ኮቴጅ ቸርች መኖርያ የደረጃ-2 ታሪካዊ ቤት ሰርተፍኬት ሰጥቶታል።
ደራሲዋ ቤቱን የገዛችው በ400 ሺህ የእንግሊዝ ፓውንድ ነው። ይህ ገንዘብ ወደ ዶላር ሲቀየር 500 ሺህ ያልፋል። ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ ሲቀየር ደግሞ ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ይሆናል፤ በግርድፉ።
ይህን ቤት ለደራሲዋ የሸጠላት የቢቢሲ ፕሮዲዩሰር የሆነው ጂሊያን መርሰር ሲሆን እሱ ራሱ ቤቱን ከደራሲዋ ወላጆች በፈረንጆች አቆጣጠር በ1995 ነበር የገዛው።

የፎቶው ባለመብት, Google
የቤቱ ሰነድ እንደሚየሳየው በፈረንጆቹ በ2011 መቀመጫውን ኤደንብራ ያደረገ አንድ ኩባንያ ቤቱን የገዛው ሲሆን ይህ ኩባንያ የተመዘገበው ደግሞ በደራሲዋ ባል በኒል ሙሬይ ስም ነው። ይህ ኩባንያ በቤቱ ላይ መጠነኛ እድሳት ለማድረግ ከዞኑ አስተዳደር ፍቃድ አግኝቷል።
ይህ ታሪካዊ እልፍኝ የቤቱ ውስጥ አሰራር ደራሲዋን ቢሊየነር ካደረጋትና የልጆች የፈንጠዚያ ልቦለድ ዘውግ ካለው ሃሪፖተር የፈጠራ ሥራ ጋር ተመሳሳይነት አለው።
ለምሳሌ በሳሎኑ ደረጃዎች ሰር ያሉት ቁምሳ ጥኖች ዋና ገጸ ባህሪው ሃሪ ቤተሰቦቹ እንዲኖርበት ካስገደዱት ቦታ ጋር ይመሳሰላል።
የልጆች ዓለምን ከዳር እስከ ዳር የወዘወዘው ይህ ዝነኛው የፈጠራ ሥራ ተቀርጾባቸዋል የሚባሉ ስፍራዎች በእንግሊዝ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከዓለም ዙርያ እየመጡ እንደሚጎበኟቸው ይታወቃል።
ምናልባት ይህም በደራሲዋ የተገዛው እልፍኝ የቱሪስት መዳረሻ የመሆን ዕድል ይኖረው ይሆናል።
ደራሲዋ ልጃገረድ ሳለች በሴድበሪ በሚገኘውና ወላጅ እናቷ ትሰራበት እንደነበር በተነገረው ዋይዲያን ትምህትር ቤት የተማረች ሲሆን፤ አባቷ ደግሞ ከብሪስትል ወጣ ብሎ በሚገኘው የመኪና አምራቹ ሮልስ ሮይስ ፋብሪካ ውስጥ ይሰራ ነበር።
የሃሪ ፖተር የፈጠራ ሥራ ውስጥ የሚገኙት ፕሮፌሰር ስናፕ እና ሮን ዊስሊ ገጸ ባህርያት መሰረታቸው ጄ ኬ በተማረችበት ዋይዲያን ትምህርት ቤት በነበሩ አስተማሪዎች ላይ እንደሆነ ይነገራል።
እሷ ድሮ የተማረችበት ዋይዲያን ትምህርት ቤት ቤተ መጻህፍቱ "ሮውሊንግ" የሚል ስም ተሰጥቶታል።
ቢሊየነሯ ደራሲ ጄ ኬ ሮውሊንግ ሃሪ ፖተርን ለመጻፍ ይህ የኖረችበት ቤት ትዝታ እንዳነቃቃት በስፋት ይነገራል።












