አዲሶቹ ተሿሚ ሚንስትሮች እነማን ናቸው?

ከግራ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ አቶ ላቀ አያሌው፣ ዶ/ር ሊያ ታደሰ እና ወ/ሮ ፈልሰን አብዱላሂ

የፎቶው ባለመብት, FBC

የምስሉ መግለጫ, ከግራ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ አቶ ላቀ አያሌው፣ ዶ/ር ሊያ ታደሰ እና ወ/ሮ ፈልሰን አብዱላሂ

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ የሚንስትር ሹመቶችን አጽድቋል። ፓርላማው የአራት ሚንስትሮችን ሹመት ያጸደቀ ሲሆን ሦስቱ ሚንስትሮች በሚንስትር ደረጃ ሲሾሙ የመጀመሪያቸው ነው።

በዚህም መሰረት አቶ ላቀ አያሌውን የገቢዎች ሚንስትር፣ ዶ/ር ሊያ ታደሰን የጤና ጥበቃ ሚንስትር፣ ወ/ሮ አዳነች አቤቤን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እና ወ/ሮ ፈልሰን አብዱላሂን የሴቶችና ሕጻናት ሚንስትር አድርጎ ሾሟል።

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከአንድ ዓመት በላይ የገቢዎች ሚንስትር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን በቅርቡ አምባሳደር ሆነው የተሾሙትን አቶ ብርሃኑ ጸጋዬን በመተካት ነው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሆነው የተሾሙት።

ተሿሚዎቹ በፓርላማው ፊት ያላቸው የሥራ ልምድና የትምህርት ደረጃ ተብራርቷል።

በዚህም መሰረት የገቢዎች ሚንስትር ሆነው የተሾሙት አቶ ላቀ አያሌው በደጋ ዳሞትና ጃቢ ጠህናን ወረዳዎች በተለያዩ ኃላፊነቶች ሠርተዋል። በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በተደረገው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በመሳተፍም በውትድርና ለሦስት ዓመታት አገልግለዋል። ከውትድርና መልስ በምዕራብ ጎጃም ዞን በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ከሠሩ በኋላ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ በመሆን ለሦስት ዓመታት አገልግለዋል።

የባህርዳር ከተማ ከንቲባ በመሆን ለሦስት ዓመት ተኩል የሠሩት አቶ ላቀ ከባህር ዳር ከንቲባነት በመቀጠል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደረጃ የክልሉ ቴክኒክ ሙያና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ለሁለት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው በመሾም ከአንድ ዓመት በላይ አገልግለዋል።

አቶ ላቀ 45 ዓመታቸው ሲሆን በሂሳብ አያያዝና በቢዝነስ አስተዳደር የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

የጤና ጥበቃ ሚንስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ሊያ ታደሰ በ1991 ዓ. ም ከጂማ ዩኒቨርሲቲ በጠቅላላ ሃኪምነት የተመረቁ ሲሆን በ1998 ዓ. ም ደግሞ በማሕጸንና ጽንስ ስፔሻሊስትነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተመርቀዋል።

የሥራ ልምዳቸውን በተመለከተ በፖሊስ ሆስፒታል፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ኮሌጅ፣ አሜሪካን አገር በሚገኝ ተቋም በሃኪምነት፣ በረዳትነትና በአመራርነት በአጠቃላይ በተለያዩ ሞያዎችና ኃላፊነቶች ከ20 ዓመታት በላይ አገራቸውን አገልግለዋል። በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም መድረኮችን በማካሄድም ያገለገሉ ሲሆን እስከ ዛሬ ደግሞ የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚንስትር ዲኤታ ሆነው አገልግለዋል። ዶ/ር ሊያ በአሁኑ ወቅት 44 ዓመታቸው ነው።

ምክር ቤቱ ለሴቶችና ሕጻናት ሚንስትር ሆነው እንዲሾሙ ያጸደቀላቸው ወ/ሮ ፌልሰን አብዱላሂ ደግሞ በእንግሊዝ ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በሳይኮሎጂ የማስተርስ ዲግሪያቸውን የተከታተሉ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውንም በእንግሊዝኛ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲዎች ተከታትለዋል።

ወ/ሮ ፈልሰን በአጎራባች ክልሎች በሰላም ዙሪያ ከወጣቶች ጋር በመሥራት ውጤት ማስገኘት የቻሉ ናቸው። በዚህ ተግባራቸውም የሰላም ሚንስቴር "የብሔራዊ የበጎ አድራጎት ፕሮግራም አምባሳደር" አድርጎ ሾሟቸዋል። ወ/ሮ ፈልሰን ዛሬ ከተሾሙት ሚንስትሮች በእድሜ ትንሿ ሲሆኑ 29 ዓመታቸው ነው።

ባለፈው ዓመት ግማሽ ሚንስትሮችን ሴት ያደረጉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ ከተሾሙት ሦስት ሴት ሚንስትሮች መካከል ሁለቱ በሚንስትር ደረጃ ሲሾሙ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።