እንግሊዝ ከአምስት አመት ባነሰ ጊዜ ሶስተኛ አጠቃላይ ምርጫ እያካሄደች ነው

የፎቶው ባለመብት, PA Media
እንግሊዛውያን ከአምስት ዓመት ባነስ ጊዜ ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ አጠቃላይ ምርጫ እያካሄዱ ነው።
ወርሀ ታህሳስ ላይ ምርጫው ሲካሄድ ይህ ከ 100 ዓመት በኋላ የመጀመሪያው ሲሆን እ.አ.አ. በ2015 እና 2017 የተካሄዱትን ምርጫዎች ተከትሎ ነው በቅርብ ዓመታት ውስጥ ሶስተኛው የሆነው።
በመላው እንግሊዝ፣ ዌልስ፣ስኮትላንድ እና ሰሜናዊ አየርላንድ የሚገኙ 650 የምርጫ ክልሎች ከሌሊቱ 11 ሰአት ጀምሮ ለመራጮች ክፍት ሆነዋል።
የምርጫ ጣቢያዎቹ ከተዘጉ በኋላ ቆጠራው ወዲያው ይጀመራል ተብሏል። ውጤቱም አርብ ጠዋት ላይ ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን ታውቋል።
650 የህዝብ ተወካዮች በዚሁ ምርጫ የሚሳተፉ ሲሆን በእያንዳንዱ ግዛት (የምርጫ ክልል) የሚያሸንፉ እጩዎች ያሸነፉበትን ክልል ወክለው በሀገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀመጣሉ።
እ.አ.አ. በ2017 በተደረገው ምርጫ ማዕከላዊ የኒውካስትል ግዛት የምርጫውን ውጤት ከሌሎቹ ከአንድ ሰአት በፊት አስቀድሞ አሳውቆ ነበር።
እንግሊዝ ውስጥ ምርጫ የሚካሄደው በአራት ወይም በአምስት ዓመት አንዴ ነው። ነገር ግን ከብዙ ዓመታት በኋላ ባለፈው ጥቅምት የህዝብ እንደራሴዎች ምርጫው ታህሳስ ላይ እንዲካሄድ ወስነዋል።
ምርጫው ታህሳስ ላይ ሲካሄድ ከ 1923 በኋላ ይኄኛው የመጀመሪያው ነው።
ማንኛውም እድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ እንግሊዛዊ በምርጫው መሳተፍ የሚችል ሲሆን የመራጮች ምዝገባ በፈርንጆቹ ሕዳር 26 ላይ ተጠናቋል።
በዚህ ምርጫ ዜጎች የመራጮች መታወቂያ ካርድ መያዝ አይጠበቅባቸውም። ስማቸውንና የመኖሪያ አድራሻቸውን በምርጫ ጣቢያው ላሉ ሰራተኞች ማሳየት ብቻ በቂ ነው።
ምርጫው ከመጀመሩ በፊት ምርጫውን የሚቆጣጠረው አካል ማንኛውም ሰው በምርጫ ጣቢያ ውስጥ ፎቶ መነሳትም ሆነ ተንቀሳቃሽ ምስል በስልኮቻቸው ማስቀረት እንደማይችሉ አስታውቋል።
በምርጫ ጣቢያዎች መገኘት ያልቻሉ ደግሞ ስማቸውንና ፊርማቸውን በመጠቀም በፖስታ ቤት በኩልም መምረጥ ይችላሉ። ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደው ምርጫ እንኳን ሰባት ሚሊየን የሚደርሱ ዜጎች ፖስታን በመጠቀም መርጠዋል።













