ማክዶናልድ ከበታች ሠራተኛው ጋር ግንኙነት መሥርቷል ያለውን ዋና ስራ አስፈፃሚ አባረረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማክዶናልድ የተሰኘው የፈጣን ምግብ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚውን ከበታች ሠራተኛው ጋር የፍቅር ግንኙነት መሥርቷል በሚል አባሮታል።
እንግሊዛዊው ስቲቭ ኢስተርብሩክ የመሠረተው ግንኙነት በፈቃድ ላይ የተመሠረተ ቢሆንምመ የኩባንያውን መመሪያ በመጣሱ ነው ሊባረር የቻለው ብሏል ድርጅቱ።
ሥራ አስፈፃሚውም ቢሆን ድርጊቱን መፈፀሙን አልካደም፤ እንዲያውም ጥፋተኛ ነኝ ሲል የበታች ሠራተኞቹን ይቅርታ ጠይቋል።
የ52 ዓመቱ ፈት ስቲቭ 1993 [በግሪጎሪ አቆጣጠር] ላይ ነበር ማክዶናልድን የተቀላቀለው። በወቅቱ ሎንዶን የሚገኘው የድርጅቱ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ሆኖ ነበር የተቀጠረው።
እስከ 2011 ከሠራ በኋላ ለቆ አንድ ሁለት ድርጅቶችን ሲያገለግል ቆየ። 2013 ግድም ዳግም ሲቀጠር የሰሜን አውሮፓ እና የእንግሊዝ ቅርንጫፎች ኃላፊ በመሆን ነበር።
ስቲቭ የማክዶናልድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆኖ የተሾመው ከአራት ዓመታት በፊት ነው። በእርሱ ዘመን ማክዶናልድ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል ትርፋማም ሆኗል ተብሎ ይነገርለታል።
ማክዶናልድ ለበታች ሠራተኞች በሚከፍለው እና ለኃላፊዎች በሚከፍለው መካከል ባለው ልዩነት ምክንያት ብዙ ይተቻል።
ስቲቭ ኢስተርብሩክ የ2018 ዓመታዊ ገቢው 15.9 ሚሊዮን ዶላር [473 ሚሊዮን ብር ገደማ] ነበር። አማካይ የበታች ሠራተኞች ዓመታዊ ገቢ ግን 7400 ዶላር ነው።
ስቲቭ የማክዶናልድ የአሜሪካ ኃላፊ በሆነው ክሪስ ካምፔዝኒስኪ ተተክቷል።















