የዓለማችን እጅግ ትርፋማው የሳዑዲ ድርጅት አክሲዮኑን ለሕዝብ ክፍት ሊያደርግ ነው

የዓለማችን እጅግ ትርፋማው የሳዑዲ ድርጅት አክሲዮኑን ለሕዝብ ክፍት ሊያደርግ ነው

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

አርማኮ የተሰኘው የሳዑዲ ነዳጅ አምራች ድርጅት አክሲዮኑን በሽያጭ ለሕዝብ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን በትዊተር ገፁ ይፋ አድርጓል።

የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ንብረት የሆነው ይህ ድርጅት ባለፈው አርብ በአረብኛ በለቀቀው መግለጫ ነው ይህንን መረጃ ያወጣው።

መረጃዎች ድርጅቱ ምናልባትም 1 ወይም 2 በመቶ ድርሻውን ብቻ ለሕዝብ ቢያቀርብ ነው ይላሉ። እንዲያም ሆኖ አክሲዮን ለሕዝብ ይፋ ከሆነ በዓለም ገበያ ትልቁ የአክሲዮን ድርሻ ይሆናል።

ምንም እንኳ የሳዑዲ መንግሥት 2 ትሪሊዮን ነው ብሎ ብሎ ቢከራከርም፤ ሳዑዲ አርምኮ 1.2 ትሪሊዮን ዶላር የሚያወጣ ድርጅት እንደሆነ ይገመታል ሲል የቢዝነስ ዜና የሚያሰራጨው ብሉምበርግ ዘግቧል።

1933 [በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር] ነበር ሳዑዲ ከአንድ የአሜሪካ ድርጅት ጋር ነዳጅ ለማውጣት የተዋዋለችው። በ1980 ደግሞ ሳዑዲ ሙሉ በሙሉ ድርጅቱን የራሷ አደረገችው።

ሳዑዲ ከቬንዝዌላ በመቀጠል በርካታ የነዳጅ ክምችት ያለባት አገር እንደሆነች ይነገራል። በምርት ደግሞ ከዩናይትድ ስቴትስ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

አርምኮ በያዝነው 2019 አጋማሽ ብቻ 46.9 ቢሊዮን ዶላር አትርፏል። በተነፃፃሪ አፕል የተሰኘው ኩባንያ 21.6 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ አጋብሷል።

ድርጅቱ አክሲዮኑን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ያስፈለገው ሃገሪቱ ነዳጅ ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ ነው ተብሏል።

አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሐማድ ቢን ሰልማን የሃገራቸው ምጣኔ ሃብት የተሰባጠረ እንዲሆን ርዕይ 2030 የሚል ዕቅድ ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ነው።

ባለፈው መስከረም ንጉሣዊው ቤተሰብ ሳዑዲ ከሌላው ጊዜ በተሻለ ነፃ አገር እንድትሆን እየሠራሁ ነው ሲል ተደምጧል። ለ49 ሃገራት ከቪዛ ነፃ ሥርዓት በመዘርጋት የቱሪዝም ፍሰቱን ለማፋጠን እየሠራሁ ነው ትላለች ሳዑዲ።

የድርጅቱ አክሲዮኑን ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ በፖለቲካ መነፅር ሲታይ ብዙ ዓይነት ቀለም አለው ይላሉ ተንታኞች። በተለይ ደግሞ ከጃማል ኻሾግጂ ግድያ በኋላ የሳዑዲ መንግሥት ከጭካኔ ጋር መያያዙን በመጥቀስ።