ኒኪ ሚናጅ ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ አልዘፍንም አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ራፐሯ ኒኪ ሚናጅ በሚቀጥለው ሳምንት ቀጠሮ ተይዞለት የነበረውን የሳዑዲ አረቢያ የሙዚቃ ድግስ ዝግጅቷ መሰረዟ ተገለጸ። ለመሰረዟ ምክንያት ያደረገችው ደግሞ በሳዑዲ አረቢያ የሴቶችንና የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን መብት አይከበርም በማለት ነው።
ኒኪ ሚናጅ በጅዳ የሙዚቃ ስራዎቿን እንደምታቀርብ ይፋ ከተደረገ ጀምሮ የተለያዩ የመብት ተሟጋቾች የሀገሪቱን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በማንሳት ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ነበር።
ሌሎች ደግሞ የኒኪ ሚናጅን ግልጥልጥ ያለ አለባበስ እያነሱና የዘፈኖቿን ግጥሞች እየጠቀሱ በዚህ ወግ አጥባቂ ማህበረሰብ ውስጥ ይህ እንዴት ይሆናል ሲሉ ይሞግቱ ነበር።
ሳዑዲ አረቢያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመዝናኛው ላይ ጥላ የነበረውን ገደብ ላላ በማድረግ ኪነጥበቡ እንዲያድግ እያበረታታች ትገኛለች።
በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የሳዑዲ ዜጋ የነበረው ጋዜጠኛ ኻሾግጂ ኢስታንቡል ውስጥ በሚገኘው የሳኡዲ ቆንፅላ ውስጥ ከተገደለ ወዲህ በሃገሪቱ ሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ በርካቶች አቃቂር ማውጣታቸውን ስራዬ ብለው ተያይዘውታል።
መጋቢት ወር ላይ ሳዑዲ 10 የሴቶች መብት ተሟጋች ሴቶችን ፍርድ ቤት መገተሯ ደግሞ የመንግሥት ተቺዎችን "ድሮም" አስብሏል።
ኒኪ ሚናጅ "ግራ ቀኙን በሚገባ ከተመለከትኩ በኋላ ጅዳ ወርልድ ፌስት ላይ ይዤው የነበረውን ፕሮግራም ሰርዤዋለሁ" ብላለች በመግለጫዋ።
"በሳዑዲ ለሚገኙ አድናቂዎቼ ስራዎቼን ማቅረብ ቢያስደስተኝም፣ በጉዳዩ ላይ ራሴን በሚገባ እውቀት እንዲኖረኝ ካደረግሁ በኋላ በሴቶች፣ በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን መብትና የመናገር ነፃነት ላይ ድጋፌን ማሳየት እንዳለብኝ ወስኛለሁ" ብላለች።
አርብ እለት መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ለሚናጅ በጅዳ የሚኖራትን የሙዚቃ ትርኢት እንድትሰርዝ ግልፅ ደብዳቤ ፅፎ ነበር።
በደብዳቤው ላይ "የመንግሥትን ገንዘብ እምቢ" እንድትልና በእስር ቤት የሚገኙ የሴቶች መብት ተሟጋቾች ጎን ለመቆም ተፅእኖ ፈጣሪነቷን እንድትጠቀም ጥሪ አቅርቦ ነበር።
ባለፈው ሳምንት የድምፃዊት ኒኪ ሚናጅ የጅዳ የሙዚቃ ድግስ እንደተሰማ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ በዓላት ላይ መገኘቷን በመጥቀስና የሳዑዲ መንግሥት በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን ላይ ያለውን አቋም በመጥቀስ አብጠልጥለዋታል።
በሳዑዲ አረቢያ የሙዚቃ ድግስ ቀጠሮ ከተያዘለት በኋላ አልፈልግም ያለችው ኒኪ ሚናጅ ብቻ አይደለችም። ማሪያ ኬሪ እንዲሁም ራፐር ኔሊ እንዲሁ ስራዎቻቸውን ሳያቀርቡ ቀርተዋል።
ለሁሉም ምክንያቱ ደግሞ ሀገሪቱ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የሚነሳባት ትችት ነው።
















