የሳኡዲው አልጋ ወራሽ የ20 ቢሊየን ዶላር ለፓኪስታን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጋዜጠኛ ኻሾግጂ አረመኒያዊ ግድያ ስማቸው በዓለም መድረክ ሲብጠለጠል የከረሙት የሳኡዲው አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን በኢሲያ ጎብኝት ላይ ናቸው።
የአልጋ ወራሹን ግዙፉ የንግድ ድጎማ ለመቀበል የመጀመርያዋ አገር ፓኪስታን ሆናለች። ፓኪስታን በንግድ ሚዛን መዛባት ናላዋ ሲዞር ቆይታለች። የአልጋ ወራሹ የ20 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ስጦታ ሰርግና ምላሽ ሆኖላታል።
ይህ የንግድ ስምምነት በነዳጅ፣ በማዕድንና በኃይል አቅርቦት ዙርያ የሚያተኩር ነው።
ፓኪስታን የውጭ ምንዛሬን በእጅጉ ስትሻ ነበር። ብሔራዊ ባንኳ በካዝናዬ የቀረኝ 8 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው ሲል ማስታወቁ አይዘነጋም። የሳኡዲ የንግድ ድጋፍ ከዚህ ፈታኝ ጊዜ ሁነኛ መውጫ ይሆናታል ተብሏል።
አልጋ ወራሹ በቀጣይነት የፓኪስታን ባላንጣ ወደሆነችው ሕንድ ያመራሉ። የሐሙስና የአርብ ጉብኝታቸው በቻይና ይሆናል።
ተንታኞች የአልጋ ወራሹ ጉብኝትና ዳጎስ ያለ ስጦታ ዓለም ሲያብጠለጥላቸው ለቆየው የጋዜጠኛ ጃማል ኻሾግጂ ጉዳይ እንደ ማድበስበሻና ስም ማደሻ ቆጥረውታል።
የአልጋ ወራሹ ጉብኝት ሕንድና ፓኪስታን በካሽሚር ጉዳይ ተቃቅረው ወደለየለት ጦርነት እንዳይገቡ በሚፈራበት ሰዓት መሆኑም ሌላው መነጋገሪያ ሆኗል።











