'የአሜሪካዊ ፉትቦል' አሰልጣኝ ቡድናቸው በሰፊ ውጤት በማሸነፉ ተቀጡ

'የአሜሪካዊ ፉትቦል' አሰልጣኝ ቡድናቸው በሰፊ ውጤት በማሸነፉ ተቀጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካዊያን 'ፉትቦል' እያሉ የሚጠሩት ስፖርት አሰልጣኝ የሆኑት ግለሰብ ቡድናቸው ተቀናቃኙን 61 ለ 13 በማሸነፉ ለጊዜው ከሥራ ታግደዋል።

የአሜሪካዋ ሎንግ አይላንድ ከተማ ትምህርት ቤት ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ሮብ ሼቨር በከፍተኛ ውጤት በማሸነፍ የከተማይቱን ሕግ ጥሰዋል ተብለው ነው የታገዱት።

ሕጉ አሸናፊ ቡድን ከ40 በላይ ነጥብ ካስቆጠረ የአሸናፊው ቡድን አሠልጣኝ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ ያዛል።

ይህ ሕጉ ከወጣ ሦስት ዓመት ሆኖታል። ዓላማው ደግሞ ስፖርታዊ ጨዋነትን ማስረፅ ነው። አሰልጣኝ ሼቨር በዚህ ሕግ የተቀጡ የመጀመሪያው አሰልጣኝ ናቸው።

የተሸናፊው ቡድን አሰልጣኝ እኔ በውጤቱም ሆነ በጨዋታው ምንም ቅሬታ አልተሰማኝም፤ አሰልጣኙም ቢሆን ምንም ስህተት አልፈፀሙም ሲሉ የሙያ አጋራቸውን ተከላክለዋል።

አጣሪ ኮሚቴው ፊት ቀርበው ለምን ቡድንዎ በሰፊ ውጤት ሲያሸንፍ ዝም ብለው ተመለከቱ? ቢያንስ ሁለተኛ ቡድንዎን አያጫውቱም ነበር ወይ? ተብለው የተጠየቁት አሰልጣኝ ሼቨር አጥጋቢ ምላሽ አልሰጡም ተብለዋል።

አሰልጣኙ ቅጣቱ ተገቢ አይደለም ብለው ቢከራከሩም ኮሚቴው አንድ ጨዋታ ሜዳ እንዳይገቡ ሲል በይኖባቸዋል።

ቅጣቱ ብዘዎችን ቢያስገርምም ወጣቶች በከፋ ውጤት ቅስማቸው እንዳይሰበር ስለሚያደርግ ተገቢ ነው ብለው የተከራከሩም አልጠፉም።

የአንድ ጨዋታ ቅጣት የተላለፈባቸው አሰልጣኝ ሼቨር የቡድናቸውን ቀጣይ ጨዋታ በአካል ተገኝተው መታደም እንዳይችሉ ታግደዋል።