የድብ መራቢያ አካል የበላው ህንዳዊ ነብር አዳኝ በቁጥጥር ሥር ዋለ

ተጠርጣሪው አዳኝ ያርለን

የፎቶው ባለመብት, Courtesy: MP Wildlife STF

የምስሉ መግለጫ, የድብ ሀሞት በዓለም ጥቁር ገበያ ከፍተኛ ገንዘብ ያስገኛል

የህንድ ፖሊስ ክትትል ሲያደርግበት የነበረውንና የድብ መራቢያ አካል ሲበላ ነበር ያለውን የእንስሳት አዳኝ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል። ግለሰቡ አርለን በመባል የሚታወቅ ሲሆን ለዓመታት ተሰውሮ ነበር።

በህንድ የፓርዲሂ ብህሊያ ጎሳዎች በጫካ ውስጥ ይኖራሉ። ኑሯቸውም የተመሠረተው በአደን ላይ ነው።

የማድህራ ፕራደሽ የደን ክፍል ኃላፊ እንዳሉት ይህ ግለሰብ አባል የሆነበት ፓርደሂ ቤሄሊያ ጎሳ አድኖ አደር ሲሆን፣ የእንስሳትን መራቢያ አካልን መብላት የወሲብ ፍላጎትን ይጨምራል የሚል እምነት አላቸው።

ግለሰቡም የተያዘው በዚያው አካባቢ ደቡባዊ ክፍል ሲሆን በአንድ ብሔራዊ ፓርክ መራቢያ አካሉ የተቆረጠ ድብ በማየታቸው የመጀመሪያ ፍንጭ እንዳገኙ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

ከአምስት ቀናት በፊት በጉጃራት ግዛት በቁጥጥር ሥር የዋለው ግለሰብ በማዕከላዊ ህንድ በነብር አደንና በሕገ ወጥ ንግድም ይታወቃል።

ግለሰቡ በማዕከላዊና ምዕራብ ህንድ ነብርን ጨምሮ የዱር እንስሳት አደንና ንግድን የተመለከቱ በርካታ ወንጀሎች ተጠርጣሪ ነው።

ትናንት ፍርድ ቤት የቀረበው ያርለንም ሆነ ጠበቃው ክሱን በተመለከ ያሉት ነገር የለም።

"እሱን ለመከታታል እና በቁጥጥር ሥር ለማዋል የተለየ ዘዴ ተጠቅመናል፤ ለስድስት ዓመታት ያህል ረጅም ክትትል ያደረግንበት ጉዳይ ነው" ሲሉ የደን ክፍል ኃላፊ ሲሮሺያ ክትትሉ ምን ያህል ፈታኝ እንደነበር አስረድተዋል።

ፖሊስ በካንሃ ብሔራዊ ፓርክ ሁለት የተሰለቡ ድቦችን በማግኘቱ ያርለን ለመጀመሪያ ጊዜ እኤአ በ2013 በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር።

ከዚያም ለአንድ ዓመት ያህል በእስር ቆይቶ በዋስ ተለቋል። ከዚያ በኋላ ግን የተለያዩ ማንነቶችን በመጠቀም ራሱን ሰውሮ ነበር የቆየው።

ሲሮሽያ እንዳሉት በግለሰቡ ላይ ስድስት የሚሆኑ ክሶች የተመሠረቱበት ሲሆን ሦስቱ ነብሮችን ማደንን የተመለከቱ ናቸው።

የድብ ሐሞት ለመቶ ዓመታት ያህል ቻይናዊያን ለባህላዊ መድሃኒትነት ይጠቀሙበት ነበር። በዚህም ምክንያት የድብ ሐሞት በዓለም ጥቁር ገበያ ሲቀርብ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ያስገኛል።

ምንም እንኳን በህንድ አደን በሕግ የተከለከለ ቢሆንም እነዚህን ጎሳዎች ጨምሮ በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም ድርጊቱ እንደቀጠለ ነው።

በአደን ላይ ለተሰማሩ ሰዎች ሕይወታቸውን የሚመሩበት አማራጭ መንገድ ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን የህንድ መንግሥት አስታውቋል።