ትራምፕ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውን ተጠቅመው ለሳዑዲ የጦር መሳሪያ ሊሸጡ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውን ተጠቅመው ለሳዑዲ አረቢያ እና ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች 8.1 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሣሪያ ሽያጭን አጸደቁ።
ሴኔቱ እና የተወካዮች ምክር ቤት የጦር መሣሪያዎቹ እንዳይሸጡ እገዳ ጥሎ ነበር።
ፕሬዝደንት ትራምፕ የሴኔቱ እና የምክር ቤቱ ውሳኔ "አሜሪካ በዓለም ላይ ያላትን ተፎካካሪነት ይቀንሳል፤ ከወዳጅ አገራት ጋር ያላትን ግነኙነትም ያሻክራል" ብለዋል።
አንዳንድ የኮንግረስ አባላት የጦር መሣሪያዎቹ በየመን ንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት ያስከትላሉ ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
አባላቱ ሳዑዲ አረቢያ በየመን በሚደረገው ጦርነት ባላት ተሳትፎና በጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ግድያ አጥብቀው ኮንነዋል።
የሪፐብሊካኑ መሪ ሚች ማኮኔል ትናንት አመሻሽ ላይ ሴኔቱ፤ ትራምፕ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውን ተጠቅመው ውድቅ ያደረጉትን ውሳኔ መልሶ ለመሻር በቀጣይ ቀናት ድምጽ ሊሰጥ ይችላል ብለዋል።
ሚች ማኮኔል ይህን ይበሉ እንጂ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፤ ትራምፕ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውን ተጠቅመው ውድቅ ያደረጉትን ውሳኔ መልሶ ለመሻር በሴኔቱ ሁለት ሦስተኛ ድምጽ መኖር አለበት። ተንታኞች የትራምፕን ውሳኔ ውድቅ ለማድረግ ይህን አብላጫ ድምጽ በሴኔቱ ማግኘት የማይታሰብ ነው እያሉ ነው።
ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውን ሲጠቀሙ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው።













