አሜሪካ፡ የሳዑዲ ልዑል በመምሰል 8ሚሊየን ዶላር ያጭበረበረው ግለሰብ ታሰረ

የፎቶው ባለመብት, Instagram/princedubai_07
አንቶኒ ጂኒያክ ለዓመታት የንጉሶችን ደረጃ የሚመጥን ቅንጡ ሆቴል ኖሯል። በጣም ውድ የሆኑ ጌጣጌጦችን ያደርጋል፤ በግል ጀቶችና ውድ መኪናዎች ይንቀሳቀሳል፤ የዲፕሎማት መንቀሳቀሻ ፍቃድም ይይዛል፤ የሚይዘው የቢዝነስ ካርድ 'ሱልጣን' ተብሎ የተፃፈበት ነበር።
ይሁን እንጂ ራሱን ልዑል ነኝ ብሎ የሚጠራው ሀሰተኛው ግለሰብ የተጋለጠው ባሳለፍነው አርብ ነበር። በዚህ የማጭበርበር ወንጀልም 18 ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፍ ተወስኖበታል።
ውሳኔውን ያሳለፈው የፍሎሪዳ ፍርድ ቤት ዳኛ "የ48 ዓመቱ ጂኒያክ አጭበርባሪ ነው፤ ራሱን የሳዑዲ ልዑል በማስመሰል ከባለሃብቶች 8 ሚሊየን ዶላር ሰብስቧል" ብለዋል።
"ላለፉት ሦስት አስርተ ዓመታትም አንቶኒ ራሱን የሳዑዲ አረቢያን ልዑል በማስመሰል በተለያዩ የአለም ክፍሎች ባለሃብቶችን ሲያጭበረብርና በእነርሱ ላይ ያልተገባ ድርጊት ሲፈፅም ቆይቷል" ሲሉ የአሜሪካ አቃቤ ሕግ ፋጃርዶ ኦርሻንም በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
ግለሰቡ በሀሰተኛ ማንነት ልዑል ካሊድ ቢን አል ሳዑዲን በመምሰል ለበርካታ ሰዎች የማይጨበጥ ተስፋ ሲሰጥ እንደነበርም ተገልጿል። ለቤተሰቦቻቸው፣ ለሥራቸው፣ አሊያም ለወደፊቱ ሕይወታቸው ያለሙ ግለሰቦችን በተስፋ ሸጧቸዋል።
በዚህም ምክንያት በርካታ ባለሃብቶች ከ8 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ አጥተዋል ሲሉ ኦርሻን አክለዋል።
አንቶኒ ጂኒያክ ማነው?
አጭበርባሪው ጂኒያክ የተወለደው ኮሎምቢያ ሲሆን የሰባት ዓመት ህፃን ሳለ በጉድ ፈቻ ወደ አሜሪካ ግዛት ሚቺጋን ተወስዷል።
የ17 ዓመት ታዳጊ ሲሆን ድርጅቶችን፣ የሱቅ ሠራተኞችንና ባለሃብቶችን ለማጭበርበር የሳዑዲውን ልዑል ገፅታን ለመላበስ ጥረት ያደርግ ነበር።
የፍርድ ቤቱ ማስረጃዎች እንደሚያትቱት ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ 11 ጊዜ ታስሮ የነበረ ሲሆን የታሰረው ከልዑል ጋር በተያያዘ ጉዳይም እንደነበር ተገልጿል።
ከአራት ዓመታት በፊት ጀምሮ ካሊድ ቢን አል ሳዑዲ የሚለውን ስም ይጠቀምበት እንደነበርም የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቢሮ ለፍሮሊዳ ግዛት አስታውቋል።
የማጭበርበር ድርጊቱን ይረዳው ዘንድም ግለሰቡ ሀሰተኛ የሆኑ የዲፕሎማት ፍቃድ እና መረጃዎችን ለጠባቂዎቹ ይገዛ ነበር፤ ይህም ብቻ ሳይሆን የሳዑዲን ባህላዊ አልባሳት ይለብሳል፤ በጣም ውድ የሆኑ ቀለበቶችንና ሰዓቶችንም ያደርግ ነበር፤ በጣም ውድ የሆኑ የጥበብ ሥራዎችንም ይሰበስብ ነበር።
በአብዛኛው ከባለሃብቶች ጋር ሲገናኝም ራሱን እንደ ልዑል አስመስሎ የሚቀርብ ሲሆን እንደ ንጉሳዊያን ቤተሰቦች ስጦታ መስጠትንም ያዘወትር ነበር።
መርማሪዎች እንደሚሉት ግለሰቡ በዓለም ላይ በተጨባጭ በሌሉ ቦታዎች ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ሲያግባባቸውም ቆይቷል።
ይሁን እንጂ የማጭበርበር ድርጊቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ በሚያሚ ቅንጡ ሆቴል ለመገንባት ያደረገው ጥረት ከሽፎበታል።
ይህ የሆነው በድርድር ላይ ሳሉ የሆቴሉ ባለቤት ግለሰቡን በመጠራጠሩ ሲሆን የአሳማ ስጋ ለመመገብ ፈቃደኛ በመሆኑም ጥርጣሬው ከፍ እንዲል አድርጎታል። "ምክንያቱም ሙስሊም ልዑል የአሳማ ስጋን አይበላም" ሲል ለሚያሚ ሄራልድ ተናግረዋል።
ከዚያ በኋላ በእርሱ ላይ ምርመራ የሚያካሂድ የምርመራ ቡድን ቀጠሩ። ይህም ወደ ፌደራል የምርመራ ቡድን አመራ።
በመሆኑም በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ጂኒያክ ገንዘብ በማጭበርበሩ፣ ሐሰተኛ ማንነት በመጠቀሙ፣ ዲፕሎማቶችን በማታለሉ ጥፋተኛ መባሉን የፍርድ ቤት ማስረጃዎች አመላክተዋል።
ኦሻር በመግለጫቸው ላይ "ፍትህ ለተበዳዮች ትጮሃለች" ሲሉ ተደምጠዋል።












