የቦይንግ 737 ማክስ ደህንነት ስለ ማሻሻል ያለው እሰጣ ገባ ቀጥሏል

Air China Boeing 737 Max 8

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቻይና ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ቀድመው ካገዱ ሃገራት መካከል ተጠቃሽ ነች

የአውሮፓ ሕብረት የትራንስፖርት ባለስልጣናት የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ደህንነትን ለማሻሻል እየተሰራ ያለውን ሶፍትዌር እውቅን ለመስጠት ከሌሎች የትራንስፖርት ባለስልጣናት ጋር አብረው እንደሚሰሩ አስታወቁ።

የአውሮፓ ሕብረት የትራንስፖርት ባለስልጣናት፤ አውሮፕላኖቹን በራሳቸው የአየር ክልል ውስጥ መልሶ ስለማብረር ውሳኔ የሚሰጡት በራሳቸው ጊዜ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ላይ የተጫነው ኤምካስ የተሰኘው ስርዓት በኢንዶኔዢያው ላየን እና ኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ላይ ለደረሰው አደጋ እንደ ምክንያትነት በርካቶች ሲያቀርቡት ቆይተዋል።

በኢትዮጵያ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ ነበር ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች እንዳይበሩ ዓለም አቀፍ እገዳ የተጣለባቸው።

የዓለማችን አየር መንገዶች የተለያዩ የትራንስፖርት ባለስልጣናት በአውሮፕላኖቹ ላይ ያላቸው መተማመን ልዩነት መፍጠር፤ በደንበኞች እና በኢንዱስትሪው ላይ አሉታዊ ጫና ያሳድራል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጣሉ።

የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች የበረራ ፍቃድ ከአሜሪካ ቀድመው ቻይና እና የአውሮፓ ህብረት መሰረዛቸው በትራንስፖርት ባለስልጣናት መካከል ባልተለመደ መልኩ ልዩነት እንዳለ አሳይቷል።

የቦይንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዴኒስ ሚልንበርግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የቦይንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኩባንያቸው ማክስ 737 አውሮፕላኖችን ወደ በረራ ለመመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የአውሮፓ ሕብረት የትራንስፖርት ኮሚሽነር ቫዮሌታ በልክ እንዳሉት፤ የአውሮፓ የበረራ ደህንነት ኤጀንሲ ቦይንግ ማክስ 737 አውሮፕላኖቹን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያቀርበውን አማራጭ በትኩረት ያጤነዋል ብለዋል።

አውሮፕላኖቹን ወደ በረራ መቼ ይመለሱ በሚለው ላይ የተቆረጠ ቀን ባይኖርም፤ ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር ግን ከሐምሌ ወር በፊት የሚሳካ አይመስለኝም ይላል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም የኢትዮጵያ አየር መንገድ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖቹን ወደ ሥራ መቼ ሊመልስ ይችላል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ ''737 ማክስ አውሮፕላኖችን ወደ በረራ ቢመለሱ፤ እኛ አውሮፕላኖቹን ለማብረር የመጨረሻው አየር መንገድ ነው የምንሆነው'' ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተው ነበር።

Ethiopian Airline crash

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የኢቲ 302 ስብርባሪ።

ከቀናት በፊት የካናዳ የአየር ትራንስፖርት ባለስልጣናት የአውሮፕላኖቹን ደህንነት በተመለከተ ከአሜሪካ ፌደራል የአቪዬሽን አስተዳደር ጋር ይልቅ ከአውሮፓ ሕብረት የትራንስፖርት ባለስልጣናት ጋር መስራትን እንደሚመርጡ ጠቁመዋል።

የትራስፖርት ባለስልጣናት የአንድን አውሮፕላን የበረራ ደህነንት ፍቃድን የሚያረጋግጡት አውሮፕላኑ ከሚመረትበት የመንግሥት አካል በሚሰጥ ማረጋገጫ ነው። በዚህም መሰረት የቦይንግ አውሮፕላኖች ደህንነት የሚያረጋግጠው የአሜሪካው የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር ነው።

ይሁን እንጂ በኢንዶኔዢያ እና በኢትዮጵያ የደረሱትን አደጋ ተከትሎ የተደረጉ ማጣሪያዎች እንዳጋለጡት የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር የአውሮፕላኖችን የደህንነት የማረጋገጥ የተወሰነውን ክፍል ለአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ሰጥቷል። ይህም በአቪዬሸን አስተዳደሩ ላይ ከፍተኛ ጫናን ፈጥሯል።

አሁንም ቢሆን ይሻሻላል የተባለው ሶፍትዌር መቼ እንደሚጠናቀቅ፣ በምን አይነት መልኩ መግባባት ላይ እንደሚደረስ እንዲሁም አውሮፕላኖቹ በረራ መቼ እንደሚጀምሩ የጠራ ነገር የለም።