ጋዛ በእስራኤል ላይ በሰነዘረችው ጥቃት የተነሳ ውጥረት ነገሰ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በእስራኤልና በጋዛ ያለው ግጭት በድጋሜ ከተቀሰቀሰ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል። የጋዛ ወታደሮች 250 የሚሆኑ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል መተኮሳቸውን የአገሪቱ ወታደሮች አስታውቀዋል።
ባለስልጣናቱ እንዳስታወቁት በተወረወረ ቦምብ አንድ እስራኤላዊ ሲገደል ከእስራኤል በተሰነዘረ ጥቃት ደግሞ እናትና ልጅን ጨምሮ አራት ፍሊስጤማውያን መገደላቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ እናትና ልጅ የተገደሉት በፍሊስጤም በተተኮሰና ዒላማውን በሳተ ሮኬት ነው ስትል እስራኤል አስተባብላለች።
ባለፈው ወር ከተደረገው የድንበር ስምምነት በኋላ የሁለቱ አገራት ቁርሾ በድጋሜ ያገረሸ ሲሆን ሁለት የእስራኤል ወታደሮች ከተገደሉ በኋላ ሁለት የሃማስ ታጣቂዎችን ጨምሮ አራት ፍሊስጤማውያን በሳለፍነው አርብ ተገድለዋል።
በግብፅና በተባበሩት መንግስታት ጣልቃ ገብነት የተደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት ወደ ጎን በመተው አሁን በቅርቡ በደረሰው ጥቃት ውጥረት መንገሱን በእየሩሳሌም የሚገኘው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ቶም ባቲማን ዘግቧል።
ጥቃቱ የተጀመረው አካባቢው መከለሉን ተከትሎ በጋዛ በተነሳ ተቃውሞ ምክንያት ሲሆን እስራኤል አካባቢውን የከለልኩት በጋዛ የሚደርሱ የጦር መሳሪያዎችን ለመቆጣጠር ነው ብላለች።
ሁለት የሃማስ ወታደሮች መገደላቸውን ተከትሎም እስራኤል በሰነዘረችው ጥቃት ሌላ ሁለት ፍሊስጤማውያን በድንበር አካባቢ መገደላቸው ታውቋል።
የፍሌስጤም ታጣቂ ሁለት የእስራኤል ወታደሮችን በድንበር አካባቢ የገደለ ሲሆን አይ ዲ ኤፍ ጥቃቱን በእስላማዊ ጂሃድ አሳቧል። እስላማዊ ጂሃድ በበኩሉ አርብ ዕለት በተፈፀመው የአፀፋ ጥቃት የሮኬት ጥቃት መፈፀሙን አምኗል።
በመግለጫውም እስራኤል ባለፈው ወር በግብፅ አሸማጋይነት የተደረገውን የተኩስ አቁም ስምምነት መጣሷንም ጨምሮ ተናግሯል።
የሃማሱ ቃል አቀባይ አብደል ላቲፍ አል ቃኑዋ " የአፀፋ ምላሹ የተሰጠው ህዝባችንን ከጥቃት ለመከላከል ነው፤ የህዝባችን ደም ፈሶ አይቀርም፤ ትግላችንም የሚቀጥል ይሆናል" ሲሉ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
በጋዛ እስራኤል ድንበሯን መዝጋቷንና የውጭ እርዳታ መቋረጡን ተከትሎ በኢኮኖሚ ችግር የሚንገላቱ 2 ሚሊዮን ፍሊስጤማውያን ይኖራሉ።













