አይ ኤስ በጀነራል ካሊፍ ጦር ላይ ጥቃት ሰነዘርኩ አለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስላማዊው ታጣቂ ቡድን (አይ ኤስ) ቅዳሜ ዕለት በካሊፍ ሃፍታር በሚመራው የጦር ቡድን መለማመጃ ካምፕ ላይ ጥቃት የሰነዘርኩት እኔ ነኝ አለ።
የሆስፒታል ምንጮች እንዳረጋገጡት አይ ኤስ በደቡባዊ ሊቢያ በምትገኘው ሳባህ ከተማ ላይ ፈጸምኩት ባለው ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል።
በጦር አዛዡ ጀነራል ካሊፍ ሃፍታር የሚመራው ጦር ከወራት በፊት በወሰደው እርምጃ በነዳጅ ሃብታቸው የበለጸጉ ደቡባዊ የሀገሪቱን ሥፍራዎች ተቆጣጥሯል።
የጀነራል ካሊፍ ጦር የሊቢያን መዲና ትሪፖሊን በቁጥጥር ሥር ለማድረግ እየተፋለሙ ይገኛሉ።
አይ ኤስ በበይነ መረብ በለቀቀው መግለጫ ትናንት አደርስኩት ባለው ጥቃት 16 ሰዎች መግደሉን ወይም ማቁሰሉን ጠቅሶ በሥፍራው በእስር ላይ የነበሩ ሰዎችንም ነጻ ማውጣቱን ጠቁሟል።
አንድ የጦር አዛዥ ለሮይተርስ ዜና ወኪል ሲናገሩ ጥቃት በደረሰበት ካምፕ ውስጥ የነበረ እስር ቤት ላይ ጉዳት መድረሱን አምነው ተጨማሪ መረጃ ሳይሰጡ ቀርተዋል።
ሃመድ አል-ካህሊይ የተባሉ የአካባቢው ከንቲባ፤ አንድ ወታደር እንደተቀላ እና ወደ ሰባት የሚጠጉ ሌሎች ወታደሮች ደግሞ በጥይት ወይም ግፍ በተሞላበት መልኩ መገደላቸውን ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።
በአካባቢው የሚገኝ የህክምና ማዕከል የሟቾች ቁጥር ዘጠኝ መሆኑን አስታውቋል።
ጀነራል ካሊፍ የሊቢያ መንግሥት ከሚቀናቀኑ ሁለት ቡድኖች መካከል ከአንደኛው ጋር ጥምረት በመመስረት የትጥቅ ትግል ላይ ይገኛሉ።
ጀነራል ካሊፍ የሊቢያ ብሄራዊ ጦር በሚሰኘው ጦራቸው አማካኝነት ከአራት ወራት በፊት ''አሸባሪዎች እና ወንጀለኛ ቡድኖች'' ባሏቸው አካላት ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል።
ከአንድ ወር በፊት ጀነራል ካሊፍ ሃፍታር ጦራቸው ወደ ዋና ከተማዋ ትሪፖሊ እንዲዘምት ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር። ይሁን እንጂ ዘመቻውን ተከትሎ ዓለም አቀፋዊ እውቅና ካለው እና በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ ከሚደረግለት የሃገሪቱ ጦር ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጠዋል።
የሊቢያ ጠቅላይ ሚንስትር ፋይዝ አል-ሴርዣ ትሪፖሊን አሳልፈው እንደማይሰጡ እና ጀነራል ካሊፍ ሃፍታር መፈንቅለ መንግሥት አውጀዋል ሲሉ ወቅሰዋል።
ሊቢያ ከ8 ዓመታት በፊት በቀድሞ መሪዋ ሙአመር ጋዳፊ ላይ ተቃውሞ ከተነሳ ወዲህ ሰላም እና መረጋጋት እርቋት ቆይቷል።












