የሊቢያ ቀውስ፡ በትሪፖሊ አቅራቢያ በተደረገ ውጊያ የ21 ሰዎች ሕይወት ጠፋ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው የሊቢያ መንግሥት በዋናው ከተማ አቅራቢያ በተደረገ ጦርነት የ21 ሰዎች ሕይወት ማለፉንና 27 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታወቀ።
የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ውጊያው በአስቸኳይ ቆሞ ሁሉም ወገኖች ወደ ንግግር እንዲመጡ ጠይቀዋል።
ጀነረራል ካሊፍ የሚመሩት አማፂ ቡድን በምስራቅ በኩል ትሪፖሊን በቁጥጥራቸው ስር ለማዋል እየገፉ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዝ አል ሲራጅ ቡድኑን መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ ሙከራ በማድረግ የወነጀሉት ሲሆን አማፂያንን በኃይል ነው የምናናግረው ሲሉ ተናግረዋል።
ሕይወታቸውን ካጡት መካከል የቀይ ጨረቃ ዶክተር ሲገኝበት የአማፂ ቡድኑ ባወጣው መግለጫም 14 ተዋጊዎቹን አጥቷል።
ቀደም ብሎ የተባበሩት መንግሥታት ለሁለት ሰዓት ያህል የተኩስ ማቆም እንዲደረግና ሰላማዊ ዜጎች ስፍራውን ለቀው እንዲወጡ የጠየቀ ቢሆንም ነገር ግን ይህ ጥያቄው ሰሚ አላገኘም።
የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር በመግለጫው ላይ "በትሪፖሊ አቅራቢያ የሚደረግ ውጊያ ያሳስበኛል" ሲል ገልጸዋል።
በመግለጫው ላይ አክሎም " በአንድ ወገን የሚደረግ የጦርነት ዘመቻ የንፁኃንን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል እና የሊቢያውያንን መፃኢ እድል ተስፋ የሚያቀጭጭ ነው" ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአለም አቀፍ ተቋማት ሰራተኞቻቸውን ፀጥታዋ እያሽቆለቆለ ከመጣው ሊቢያ እያስወጡ ነው።
ሐሙስ ዕለት ጀምሮ ጀነራል ካሊፍ ሃፍተር የሚመሩት ጦር ከደቡብና ከምዕራብ በኩል ጦርነቱን አፋፍሞታል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ እንዲያስችለው ያቀረበው የተኩስ አቁም ጥሪ ሰሚ ጆሮ አለማግኘቱን የጠቀሰ ሲሆን ሌሎች የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ወደ ጦርነት ቀጠናው ለመግባትና ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል እንደተናገሩት አሁንም ቢሆን በጎ ምላሽ እንደሚያገኙ ተስፋ አላቸው።
እሁድ እለት የአማፂ ቡድኑ የመጀመሪያውን የአየር ላይ ጥቃት ማድረጉን አስታውቋል። ይህ የሆነው ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው መንግሥት ቅዳሜ እለት የአየር ላይ ጥቃት ካደረሰባቸው በኋላ ነው።
ሊቢያ ለረዥም አመት ያስተዳደሯት ሙሀመድ ጋዳፊ በ2011 ከስልጣን መውረድና መገደል በኋላ ሰላምና መረጋጋት ርቋት ትገኛለች።












