የ737-8 ማክስ መከስከስ ለቦይንግ ምን ማለት ነው?

የፎቶው ባለመብት, Jonathan Druion
በአቪዬሽን ዓለም ሃያል የሆነው ቦይንግ ከባድ ቀውስ ውስጥ ይገኛል።
ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላኑ ላይ ያሻሻለው ሲስተም ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኑ አደጋ ምክንያት መሆኑን የሚያሳየው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት በመርማሪዎች ከተረጋገጠ ነገሩ ለቦይንግ ትልቅ ፈተና ይሆናል።
የዚህኛው አውሮፕላን አደጋ መንስኤ ከአምስት ወራት በፊት ከተከሰከሰው ከላየን አየር መንገዱ ማክስ አውሮፕላን ጋር እየተመሳሰለ መሆኑ ደግሞ በቦይንግ ላይ ነገሮችን ይበልጥ ያከብዳል።
የሁለቱ ማክስ አውሮፕላኖች አደጋ ምርመራ ሳይጠናቀቅ ገና የቦይንግ ችግሮች አንድ አንድ እያሉ እተደራረቡ ነው።
ችግሩ ያለው የት ነው?
የአውሮፕላኑን አፍንጫ ወደ ታች በመድፋት የአደጋው ምክንያት ሆኗል እየተባለ ያለው ቦይንግ በአውሮፕላኑ ላይ ያሻሻለው ስርዓት ነው።
ይህ ስርዓት የሚሰራው በማክስ አውሮፕላኖች ከፊት ለፊት በአንድ በኩል ከሚገኝ ምልክት ሰጭ (ሴንሰር) በሚያገኘው መረጃ ላይ ተመስርቶ ነው።
የላየኑ አየር መንገድ አውሮፕላንም በዚህ መልኩ በሄደ የተሳሳተ መረጃ አፍንጫው ወደ ታች እየተደፋ በተነሳ በጥቂት ደቂቃዎች መከስከሱ ተገልጿል።
እስከ አሁን ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት የኢትዮጵያ አየር መንገዱ አውሮፕላን አደጋም በተመሳሳይ ምክንያት የደረሰ ነው።
በተነሱ በደቂቃዎች ውስጥ የተከሰከሱት የላየንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች አፍንጫ በተደጋጋሚ ከቁጥጥር ውጭ ወደ ታች ሲል እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
የሁለቱም አውሮፕላኖች አብራሪዎች አውሮፕላኑን ቀና ለማድረግ ቦይንግ ያስቀመጠውን መመሪያ ቢተገብሩም አውሮፕላኖቹን መታደግ አልቻሉም።
የቦይንግ 737 የቴክኒክ መመሪያ አዘጋጅ የሆኑት ካፒቴን ብራዲ በሁለቱ አውሮፕላኖች አደጋ ዙሪያ እያጠነጠነ ያለው ነገርና ውዝግብ ሊታዩ የሚገባቸው ዝርዝር ጉዳዮች መኖራቸውን ያመለክታል ይላሉ።
ዝርዝር ጉዳዮች የሚሏቸው የአውሮፕላኑ የበረራ ብቃት፣ የአደጋ ተጋላጭነት፣ ቁጥጥር፣ አጠቃለይ ስልጠና፣ የፓይለቶች ማሰልጠኛ መመሪያ የመሰሉትን ያካትታል።
የቦይንግ ቀጣይ የህግ ፈተናዎች?
በአሁኑ ወቅት ቦይንግ ላይ የተለያዩ ምርመራዎች እየተካሄዱ ሲሆን ሁለት ክሶችም ተመስርተውበታል። ሌሎች ክሶችም ይቀጥላሉ ተብሎ ይገመታል።
የመጀመሪያው ክስ የተመሰረተው በተደጋጋሚ ለአሜሪካ ፕሬዘዳንትነት በተወዳደሩትና በአደጋው የ24 ዓመት የቅርብ ዘመዳቸውን ባጡት ራልፍ ናደር ነው።
ባለፈው ሳምንት ደግሞ ከመንገደኞች ውስጥ አንዱ የነበረው ሩዋንዳዊ ጃክሰን ሙሶኑ ቤተሰቦች በችካጎ ቦይንግ ላይ ክስ መስርተዋል።
የክሱ ጭብጥም ቦይንግ ያሻሻለው ስርዓት እንከን ያለው መሆኑን ያስቀምጣል።
ቦይንግ ምን እያደረገ ነው?
ቦይንግ መጀመሪያ ለማክስ አውሮፕላን እንዲሁም አውሮፕላኑ ላይ ላደረገው ማሻሻያ ያገኘው ሰርተፍኬት ላይ ምርመራ ይከፈታል።
የቀድሞ የቦይንግ የሙከራ አብራሪ በሺህ የሚቆጠሩ የሙከራ የበረራ ሰዓታትን የሚመለከቱ መረጃዎች ዳግም እንደሚመረመሩ ተናግሯል።
አደጋውን ተከትሎ ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላኑ ላይ ተጨማሪ አደጋ አስጠንቃቂ ስርዓቶችን እንደሚጨምርና የፓይለቶች ስልጠና መመሪያውንም እንደሚያሻሽል አስታውቋል።
ነገር ግን ይህኛው የቦይንግ ማሻሻያ የሚመለከታቸውን የአቪዬሽን ተቆጣጣሪ አካላት ይሁንታ በቀላሉ የሚያገኝ አይሆንም።
እንደ አውሮፓ አቪዬሽን ደህንነት ኤጀንሲ ያሉ ከአሜሪካ ውጭ ያሉ ተቆጣጣሪ አካላትም ነገሩን በንቃት የሚከታተሉት ሲሆን በነገሮች እርግጠኛ ሳይሆኑ ማክስ ዳግም በአውሮፓ የአየር ክልል እንዲበር ሊፈቅዱ አይችሉም።
ቦይንግ ምን ያህል ይከስራል?
በመቶዎች የሚቆጠሩ ማክስ አውሮፕላኖቹ እንዳይበሩ የታገዱበት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ማክስ አውሮፕላኖቹ ግዥ ውሎቹ ውሃ የበላቸው ቦይንግ ያጋጠመው የገበያ ቀውስ ገና ተጀመረ እንጂ አላለቀም።
ማክስ አውሮፕላኖቻቸው እንዳይበሩ የታገዱባቸው አየር መንገዶች ከቦይንግ ካሳ መፈለጋቸው አይቀሬ ነው።
እገዳው ፀንቶ የሚቆይ ከሆነ የቦይንግ እዳ እየናረ መሄዱንም ይቀጥላል። ቢሆንም ግን ቦይንግ የገንዘብ ሃያል ነው። የቀድሞ የቦይንግ በረራ ኢንጅነር ፒተር ሊሜ አሁን ከፊቱ የተጋረጠው ኪሳራ ቦይንግን ክፉኛ በሚባል ደረጃ የሚጎዳው እንዳልሆነ ይናገራሉ።
የኩባንያውን መልካም ስም እንደሚያበላሸው ግን ያምናሉ። ዳግም ማክስ አውሮፕላንን አየር ላይ መመለስም ቀላል እንደማይሆን ይገልፃሉ።
በአቪዬሽን አለም ቁልፉ ነገር ደህንነት በመሆኑ "አሁን ተቆጣጣሪዎቹን በእርግጠኝነት ምን እንደሚያሳምናቸው አይታወቅም" ብለዋል።
ቦይንግም ደህንነት ሁሌም ትኩረት የሚያደርግበት ቀዳሚ ነገር እንደሆነ በተደጋጋሚ ተናግሯል።













