አውሮፕላኑ 'ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ነበር'

የአደጋው መርማሪዎች በአደጋው ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኢትዮጵያ አውሮፕላን ከመውደቁ በፊት በርካታ ጊዜ የአፍንጫ መደፈቅ ገጥሞት እንደነበር የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ አመልክቷል።

ባለስልጣናት እንደገለጹት አብራሪዎቹ አውሮፕላኑን ለማትረፍ በተደጋጋሚ የቦይንግን መመሪያ ተከትለው ጥረት አድርገዋል። የትራንስፖርት ሚንስትሯ ዳግማዊት ሞገስ "አብራሪዎቹ ጥረት ቢያደርጉም ሊቆጣጠሩት ግን አልቻሉም፤ አደጋው እንዳይከሰትም አብራሪዎቹ ሁሉንም ማድረግ የሚገባቸውን ጥንቃቄ አድርገዋል" ብለዋል።

ሪፖርቱ ስለአውሮፕላኑ መከስከስ ምን ይላል?

የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ማንንም ተወቃሽ አላደረገም። ሌሎች ዝርዝር መረጃዎችንም ከመስጠት ተቆጥቧል፤ ነገር ግን ቦይንግ የአውሮፕላን መቆጣጠሪያ ሥርዓቱን ማስተካከል እንዳለበትና የአቪየሽን ባለስልጣናት ደግሞ ቦይንግ 737 ማክስ ከመብረሩ በፊት ሁሉንም ችግሮቹን መፍታቱን ቢያረጋግጥ መልካም ነው የሚል ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወልደ ገብረማርያም አብራሪዎቹን እጅግ የሚኮሩባቸውና ከፍተኛ የሙያ ክህሎት ያላቸው ቢሆኑም እንዳለመታደል ሆኖ ግን የአውሮፕላኑን ከመከስከስ ሊያተርፉት አልቻሉም ብለዋል።

የአውሮፕላኑ የበረራ መቆጣጠሪያ እንዴት እንደሚሰራ ስዕላዊ መግለጫ

የሪፖቱ ውጤት ለቦይንግ ምን ትርጉም ይኖረዋል?

በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሁለት የመከስከስ አደጋ አጋጥሞ 346 ሰዎች ሞተዋል። ሁለቱም የመጀመሪያ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት የቦይንግ 737 ማክስ አዲሱ ስሪት አገልግሎት መስጠት ማቆሙንና አውሮፕላኑ በተደጋጋሚ የአፍንጫ መደፈቅ ገጥሞታል። ሁለቱም አደጋዎች ላይ አንድ አይነት ሃሳብ ነው የሚነሳው።

በአደጋው ዘመድ ወዳጆቻቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥርን መገመት ሊያዳግት ይችላል። ነገር ግን አምራቹ ኩባንያ ምን ያህል ትርፍ ሊያጣ እንደሚችልና ዝናው ዝቅ እንደሚል መገመት ይቻላል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል። በርካታ ትዕዛዞችም ተሰርዘዋል፤ ወደፊትም እንዳይታዘዝ ተጽዕኖ አሳድሯል።

ቦይንግ በተፎካካሪው ኤር ባስ የተሰራውን ዘመናዊ እና ነዳጅ ቆጣቢ የሆነውን A320 ለመገዳደር ታሳቢ አድርጎ ነበር 737 ማክስን ለገበያ ያቀረበው። ይሁን እንጅ አንድ 737 አውሮፕላንን በማብረር ልምድ ያለው አብራሪ እንደገለጸው ለኤር ባስ ምላሽ ተብሎ የተሰራው አዲሱ አውሮፕላን ሁለቱን አደጋዎች ያስከተለና 'እንከን' ያለበት ነው።

ቦይንግ ችግሩን ለማስተካከል እየሰራ ነው። አውሮፕላኑ የደህንነት ማረጋገጫ አግኝቶ አየር ላይ የሚወጣበትን መንገድ መፈለግም ይኖርበታል።

ለመሆኑ ከአደጋው በኋ ቦይንግ ምን አደረገ?

ቦይንግ ለአብራሪዎች አውሮፕላኑን እንዴት መቆጣጠር እንዳለባቸው የበረራ ደህንነት መመሪያ አስተላልፏል።

ለሁሉም ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ካሁን በፊት እንደ አማራጭ ያገለግሉ የነበሩትን ተጨማሪ የማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችን አዘጋጅቷል።

ቦይንግ 737 ማክስን የመረዳት አቅምን ለማሳደግ የሚያስችል ስልጠናም እያዘጋጀ ነው።

ይህ ማለት ግን አውሮፕላኑ የተከሰከሰው ችግር ስላለበት እንዳልሆነ ቦይንግ ይከራከራል።