ከኢቲ 302 አደጋ ጋር በተያያዘ ኬንያውያን የኢትዮጵያ አየር መንገድንና ቦይንግን ሊከሱ ነው

ኢቲ 302

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢቲ 302 ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ተሳፍረው በአደጋው ህይወታቸውን ያጡ ኬንያውያን ቤተሰቦች ከአደጋው ጋር በተያያዘ አየር መንገዱንና ቦይንግን እንከሳለን አሉ።

ከሟቾቹ 157 ሰዎች መካከል 32ቱ ኬንያውያን ነበሩ። የሟቾች ቤተሰቦች እንደሚሉት ከሆነ አየር መንገዱ እና ቦይንግ ለመሞታቸው ኃላፊነቱን መውሰድ አለባቸው።

የሟች ቤተሰቦች ኬንያ እና አሜሪካ በሚገኙ የጠበቃ ቡድን የተወከሉ ሲሆን ክሱም የሚመሰረተው በሃገረ አሜሪካ እንደሚሆን ታውቋል።

ከዚህ ቀደምም በአደጋው ህይወቱ ያለፈው ሩዋንዳዊ ጃክሰን ሙሶኒ ዘመዶች በአሜሪካ ቦይንግን መክሰሳቸው ይታወሳል። በክሳቸው ላይ አደጋ የደረሰበት ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን በአውቶማቲክ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓቱ ላይ የዲዛይን ችግር አለበት ሲሉ አመልክተዋል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአደጋው በኋላ

ቦይንግ ከኢንዶኔዢያው ላየን አየር መንገድ ጋር በተያያዘም ከሟች ቤተሰቦች በርካታ ክሶች ቀርበውበታል።