ኬንያዊው ጋዜጠኛ የ2018 የቢቢሲ ኮምላ ዱሞር ሽልማትን አሸነፈ

ዋይሂጋ ምዋራ

የፎቶው ባለመብት, Joshua Wanyama

ኬንያዊው ጋዜጠኛና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጁ ዋይሂጋ ምዋራ ቢቢሲ በየአመቱ የሚያዘጋጀውን የኮምላ ዱሞር ሽልማት አሸናፊ ሆኗል።

ጋዜጠኛው በኬንያ ''ሲቲዝን ቲቪ'' በተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ ውስጥ እጅግ በጣም ተወዳጅ የሆነ ''ኒውስ ቡሌቲን'' የተባለ ፕሮግራም አቅራቢ ነው።

ከሚያገኘው ሽልማት በተጨማሪም ለንደን በሚገኘው የቢቢሲ ዋና መስሪያ ቤት ለሶስት ወራት ቆይታ የሚያደርግ ሲሆን፤ ወደ ሃገሩ ተመልሶም ስለነበረው ቆይታና ያገኘውን ልምድ የሚያካፍል ይሆናል።

ቢቢሲ ሽልማቱን በየዓመቱ ለማዘጋጀት የወሰነው ታዋቂው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ኮምላ ዱሞር እ.አ.አ በ2014 በድንገት ከሞተ በኋላ እሱን ለማስታወስ ያለመ ነው።

ዋይሂጋ ምዋራ ሽልማቱን ሲያሸንፍ አራተኛው ሰው ሲሆን፤ በ2015 የተዘጋጀው የመጀመሪያውን ሽልማት ዩጋንዳዊቷ ናንሲ ካቹንጊራ፤ በተከታዮቹ ሁለት ዓመታት ደግሞ ናይጄሪያውያኑ ዲዲ አኪንዬሉሬ እና አሚና ዩጉዳ አሸናፊ ሆነዋል።

ዋይሂጋ በኬንያውያን ዘንድ ተወዳጅና ከፖለቲካ እስከ ስፖርት ድረስ ሁሉንም ዘገባዎች የሚያቀርብ ጋዜጠኛ ነው።

''ኮምላ ዱሞር ብዙ ነገር ያስተማረኝና የተዋጣለት ጋዜጠኛ ነበር፤'' እሱ በህይወቱ ማከናወን ከቻለው 20 በመቶ እንኳ የሚሆነውን ማሳካት ብችል በህይወቴና በጋዜጠኝነት ሙያ ብዙ እንደሰራሁ ነው የምቆጥረው።'' ብሏል ዋይሂጋ።