ከፈረንሳዩ ሙዚየም ውድ ቅርሶችን በመስረቅ የተጠረጠሩ አምስት ተጨማሪ ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ከሉቭር ሙዚየም ጌጣ ጌጦቹ የተሰረቁት ጥቅምት 9 2018 ዓ.ም. እሁድ ዕለት ነበር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ከሉቭር ሙዚየም ጌጣ ጌጦቹ የተሰረቁት ጥቅምት 9 2018 ዓ.ም. እሁድ ዕለት ነበር

አምስት ተጨማሪ ተጠርጣሪዎች በሉቭር ሙዚየም ስርቆት ላይ ባላቸው ተሳትፎ የተነሳ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፈረንሳይ አቃቤ ሕግ አስታወቀ።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በፓሪስ ረቡዕ ምሽት መሆኑ ተገልጿል።

እነዚህ አምስት ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች የተያዙት ከዚህ በፊት የተያዙት ሁለት ተጠርጣሪዎች "በከፊል ያላቸውን ተሳትፎ" ካመኑ በኋላ ነው።

በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል ሦስቱ ስርቆቱን ከፈጸሙት አራት ግለሰቦች መካከል መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን በቀጥታ በወንጀሉ ላይ የተሳተፈው አራተኛው ግለሰብ እስካሁን ድረስ አልተያዘም።

የፈረንሳይ መርማሪዎች ስለ ወንጀለኞቹ እና ስለነበራቸው ተሳትፎ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ነገር ግን አቃቤ ሕግ ለአንድ የሬዲዮ ጣቢያ ሐሙስ ዕለት በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ሰዎች መካከል የአንዱ ዲኤንኤ ከወንጀሉ አካባቢ ከተሰበሰበው ጋር ይያያዛል ብሏል።

አዲስ በቁጥጥር የዋሉት አራቱ ሰዎች በስርቆቱ ላይ የነበራቸው ሚና ግልጽ ባይሆንም፣ አቃቤ ሕግ ግን "ወንጀሉ እንዴት እንደተቀነባበረ እና እንደተፈጸመ ይነግሩን ይሆናል" ብሏል።

የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ውድ ቅርሳ ቅርሶቹን በመዝረፍ ላይ በቀጥታ የተሳተፉት በአካል ከሰረቁት ሰዎች የበለጠ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አዲሶቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ክስ ሳይመሰረትባቸው ወይንም ሳይለቀቁ እስከ አራት ቀን በእስር ቤት ሊቆዩ ይችላሉ።

በፈረንሳይ ፓሪስ በጎብኚዎች በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጎበኘው ሉቭር ሙዚየም 102 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ቅርሳ ቅርሶች የተሰረቁት ጥቅምት 9 2018 ዓ.ም. እሁድ ዕለት ነበር።

ከሙዚየሙ የተሰረቁት በዕንቁ እና በወርቅ የተንቆጠቆጡት ውድ ጌጣ ጌጦች እስካሁን ድረስ አልተገኙም።

ከዚህ ቀደም የወንጀል ታሪክ የነበረባቸው እና እድሜያቸው በ30ዎቹ የሚገመት ሁለት ተጠርጣሪዎች መጀመርያ ላይ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን ወደ ሙዚየሙ ለመግባት መስኮቱን በመሳሪያ የሰበሩት እና የተወሰኑ ጌጣጌጦችን የሰረቁት ግለሰቦች እንደሆኑ ይታመናል።

እነዚህ ተጠርጣረዎች ባለፈው ሳምንት ወደ እስር ቤት ተወስደዋል።

የፈረንሳይ አቃቤ ሕግ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሰዎች መካከል አንዱ ወደ አልጄሪያ ለመብረር ሲል የተያዘ መሆኑን ገልጸው ሌላኛው ግን ፈረንሳይን ለመልቀቅ ሃሳብ አልነበረውም ብለዋል።

እስካሁን ድረስ ስርቆቱ በሙዚየሙ ውስጥ ከሚሰሩ ሰዎች ጋር በመመሳጠር የተፈጸመ ለመሆኑ የተገኘ መረጃ የለም ሲሉ አቃቤ ሕጓ ተናግረዋል።

ስርቆቱ በተፈጸመበት ዕለት ሌቦቹ ማለዳ 3፡30 ላይ ሙዚየሙ ለጎብኚዎች ክፍት ሲሆን የደረሱ ሲሆን ጌጣ ጌጦቹ ወደ ተቀመጡበት ጋሌሪያ ዲ አፖሎን በረንዳ ከመኪና ላይ በተዘረጋ መሰላል ወጥተዋል።

ሌቦቹ የጋለሪውን መስኮት በመሳሪያ ተጠቅመው በመቁረጥ ሰብረው ወደውስጥ በመዝለቅ ዘረፋውን ፈጽመዋል።

እንደ ፈረንሳይ አቃቤ ሕግ መረጃ ከሆነ ሌቦቹ በጋለሪ ውስጥ ለአራት ደቂቃ ብቻ የቆዩ ሲሆን፣ ለማምለጥ አነስተኛ ሞተር ሳይክል፣ ስኩተር፣ ተጠቅመው ከሄዱ በኋላ በመኪና ቀጣይ ጉዟቸውን አድርገዋል።

ዘረፋው ከተፈጸመ በኋላ በሙዚየሙ እና በሌሎች የፈረንሳይ የባህል ተቋማት ያለው ጥበቃ የተጠናከረ ሲሆን በሉቭር የሚገኙ የተወሰኑ ውድ ጌጣ ጌጦች ወደ ፈረንሳይ ባንክ እንዲዛወሩ ተደርገዋል።