በዓለማችን ውድ ሃብቶች እና ቅርሶች ላይ የተፈጸሙ ዋና ዋና ዝርፊያዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጥቅምት 9/2018 ዓ.ም. በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ የማይታሰበው ስርቆት የተፈጸመው ፀጥ ባለው እሁድ ጠዋት ላይ ነበር።
የዘራፊዎች ቡድን በዚያ ውብ ማለዳ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሚመጡ ቱሪስቶች በብዛት የሚጎበኘውን ሉቨር ሙዚየምን ሰብረው በመግባት በዋጋ የማይተመን ትልቅ ታሪካዊ ፋይዳ ያላቸውን የንጉሣውያን ጌጣጌጦችን ሰረቁ።
ይህ ዘረፋ የፈራንሳይ ሕዝብን እና ባለሥልጣናትን በእጅጉ አስደንግጦ ሌቦቹን ለመያዝ ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ሳምንት ሊሆነው ነው።
በዓለም ላይ በጣም ውድ እና ታሪካዊ የሆኑ ሃብቶች ከደኅንነት ዕይታ ተሰውረው በሌቦች እጅ ሲወድቁ ይህ የመጀመሪያው አልነበረም።
በሜክሲኮ ፊልም ከሚመስለው እና በጣም ድፍረት ከታየበት ዝርፊያ ጀምሮ በጀርመን በሚገኘው የንጉሣዊ ቤተ መንግሥት ላይ በጥንቃቄ ታቅዶ እስከ ተፈጸመው ስርቆት ያለውን ቢቢሲ እንዲህ አጠናቅሯል።
የሜክሲኮ 'የክፍለ ዘመኑ ዘረፋ'

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1985 የገና ዋዜማ፣ አብዛኞቹ ሜክሲኳውያን ከሚወዷቸው ዘመዶቻቸው ጋር ጊዜያቸውን በሚያሳልፉበት ወቅት፣ ሁለት ሰዎች በአገሪቱ ዋና ከተማ ወደሚገኘው ብሔራዊ ሙዚየም የአየር ማስተላለፊያ ቱቦውን ተጠቅመው እየተሳቡ ገቡ።
ከ100 በላይ በዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ የማያን ንጉሥ ፓካል የፊት ጭንብልን ጨምሮ፣ የማያን እና የዛፖቴክ ቅርሶችን ሰርቀዋል።
በዘረፋው የአገሪቱ ባለሥልጣኖች ግራ ተጋብተዋል።
መጀመሪያ ላይ ከስርቆቱ ጀርባ የኪነ ጥበብ ኮንትሮባንድ ነጋዴዎች እጅ እንዳለበት እርግጠኞች ነበሩ።
በ48 ሰዓታት ውስጥ ባለሥልጣናቱ በአገር አቀፍ ደረጃ የፀጥታ ጥበቃውን አጠናከሩ። እናም በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ሊሸጥ የሚችል ማንኛውም ዓይነት ቅርስ ላይ ክትትል አደረጉ።
በወቅቱ "የዘረፉት ነገር ለድርድር የማይቀርብ እና በዋጋ ሊተመን የማይችል የአንትሮፖሎጂ ዋጋ ያለው የታሪካችን ክፍል ነው" ሲሉ የብሔራዊ አንትሮፖሎጂ ተቋም ባልደረባ ፌሊፔ ሶሊስ ተናግረዋል።
የ21 ዓመቶቹ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎቹ ካርሎስ ፔርቼስ እና ራሞን ሰርዲና ከዚህ ወንጀል ጀርባ እንደ ነበሩበት በወቅቱ አልታወቁም ነበር።
ለስድስት ወራት ያህል ከ50 ጊዜ በላይ ሙዚየሙን በመጎብኘት የደኅንነት ሥርዓቱን በማጥናት ለዘረፋው ሲዘጋጁ ቆይተዋል።
ከአራት ዓመት በኋላ በአውሮፓውያኑ ሰኔ 1989 ፖሊስ አንዳንድ የተሰረቁትን ቅርሶች በፐርቼስ እጅ አገኘ። አንዳንዶቹን በአካፑልኮ ለሚገኝ የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪ ለመሸጥ ሞክሮ ነበር።
ፐርቼስ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን፣ ነገር ግን የወንጀል አጋሩ የሆነው ሰርዲና እስከ ዛሬ ድረስ ከፖሊስ ዕይታ እንደተሰወረ ነው።
አብዛኛዎቹ ቅርሶች ወደ ሙዚየሙ ተመልሰው ዳግም በአውሮፓውያኑ ሰኔ 1989 ለዕይታ ቀርበዋል።
በዚህ ምክንያት አዳዲስ ጥብቅ የደኅንነት እርምጃዎች ሲወሰዱ የጥበቃዎች ቁጥርም ጨምሯል።
የጠፋው የቦስተን ቅርስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውሮፓውያኑ መጋቢት18/1990 ጠዋት ላይ፣ እንደ ቦስተን ፖሊስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በኢዛቤላ ስቱዋርት ጋርድነር ሙዚየም ደረሱ። ላገኟቸውም የጥበቃ አባላት ሁከት መፈጠሩን ሪፖርት መደረጉን እና ለዚያ ምላሽ ለመስጠት መምጣታቸውን አሳወቁ።
ሁኔታውን ምንም ያልተጠራጠሩት ጠባቂዎች ወደ ውስጥ እንዲገቡ ፈቀዱላቸው።
በደቂቃዎች ውስጥ ሙዚየሙ የወንጀል ማዕከል ሆነ።
ጠባቂዎቹ እጅ እግራቸው ታስሮ ወደ ምድር ቤት ተወሰዱ። ሌቦቹ በ81 ደቂቃ ውስጥ 13 ድንቅ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ለመዝረፍ በፍጥነት ተንቀሳቅሰዋል።
በዚህ ዘረፋ አይተኬ የሆኑ የአውሮፓ ስመ ጥር ሠዓሊያን ሥራዎች እንደ ኤድጋር ዴጋስ፣ ኤድዋርድ ማኔት እና የሬምብራንት ብቸኛው የባሕር ገጽታ የሚያሳይ (ዘ ስቶርም ኦን ዘ ሲ ኦፍ ጋሊሌ) ሥራን ጨምሮ 500 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የጥበብ ሥራዎች ተሰረቁ።
እስከዛሬ ድረስ ጉዳዩ እልባት አላገኘም።
በዚህ ዘረፋ ላይ እስካሁን ድረስ የሚደረገው ምርመራ ፋይል አልተዘጋም። ሙዚየሙ የጥበብ ሥራዎችን ያሉበትን ለሚጠቁም 10 ሚሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብቷል።
እንደ ሙዚየሙ ድረ ገጽ መረጃ ከሆነ፣ ይህ ገንዘብ በግል ተቋም ቃል የተገባ ትልቅ ጉርሻ ነው።
በጋለሪው ግድግዳዎች ላይ አሁንም ባዶ ፍሬሞች ለተፈጸመው ስርቆት ምስክር ሆነው ተንጠልጥለው ይገኛሉ።
የድሬዝደን የአልማዝ ጌጥ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአውሮፓውያኑ ኅዳር 25/2019 ጎህ ሲቀድ በጀርመን ድሬዝደን ቤተ መንግሥት አቅራቢያ የእሳት ቃጠሎ ተነሳ። የአደጋ ጊዜ መብራቶች ብልጭ ድርግም ሲሉ እና የኤሌትሪክ ኃይል ሲቋረጥ መጨላለሙን በመጠቀም ዘራፊዎች መንቀሳቀስ ጀመሩ።
በደቂቃዎች ውስጥ፣ የዘራፊዎች ቡድን በመስኮት በኩል ሾልከው በመቶዎች የሚቆጠሩ ውድ ጌጣ ጌጦችን እና አልማዞችን ወደያዘው፣ የ18ኛው ክፍለ ዘመን አውግስተስ ዘ ስትሮንግ ውድ ሃብት ወደተቀመጠበት ታሪካዊው ግሪን ቮልት ገቡ።
ሌቦቹ እሳቱን ትኩረት ለመቀየር በሚል ሆን ብለው ያስነሱት ነበር። ከዚያም የመስኮቱን ፍርግርጎች በብረት መቁረጫ ቆርጠው በማንሳት ወደ ውስጥ ዘለቁ።
መዝረፍ የፈለጉት ከ18ኛው እና 19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተከማቹትን 21 የንጉሣዊ ውድ ቅርሶች ነው።
ከተዘረፉት መካከል በንጉሣዊ ሥርዓት ወቅት የሚያዝ ሰይፍ፣ በእንቁ የተሸለሙ ትከሻ ላይ የሚቀመጡ ማዕረጎች፣ ቲያራ እና በአንድ ላይ በ4,300 የከበሩ ድንጋዮች የተዋቡ አዝራሮች ናቸው።
መቀመጫውን በበርሊን ያደረገው የወንጀል ቡድን ከ10 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ዘረፋውን አጠናቅቋል።
ማምለጫቸው እንደ መግቢያቸው ሁሉ በጥንቃቄ የተሰላ ነበር። አሻራቸውን ለመደበቅ እንዲያስችላቸው በክፍሉ ውስጥ የእሳት ማጥፊያ ረጩ። ከዚያም በመኪና አምልጠዋል። በኋላ ላይ ተሽከርካሪውን በመኪና ማቆሚያ ውስጥ አስቀምጠው እሳት ከለኮሱበት በኋላ ወደ በርሊን አምልጠዋል።
በአውሮፓውያኑ 2023 ከዚህ ስርቆት ጋር በተያያዘ አምስት ሰዎች ከአራት እስከ ስድስት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል።
በአልማዝ የተሸለመው ጎራዴን ጨምሮ አንዳንድ ጌጣጌጦች ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ተገኝተዋል።
ነገር ግን 12 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ 'ዋይት ስቶን ሾፍ ሳክሶኒ' የተባለ ብርቅዬ አልማዝን ጨምሮ በርካታ ጌጣጌጦች እስከ አሁን አልተገኙም።
ግሪን ቮልት የተመለሱትን ቅርሶች እና የዝነኛውን ወንጀል ቦታ ለማየት ለሚፈልጉ ጎብኚዎች ክፍት ነው።
የኢራን ውድ ሃብቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቴህራን ጎዳናዎች ቁልቁል ሲወርዱ፣ ከብረት በሮች ጀርባ በደንብ የታጠቁ ፖሊሶች ስር፣ የብሔራዊ ቅርሳ ቅርስ ግምጃ ቤት አለ።
ክምችቱ ለዘመናት የተሰበሰበው በሳፋቪድ፣ አፍሻሪድ፣ ቃጃር እና ፓህላቪ ሥርወ መንግሥት ሲሆን፣ በዓለም ላይ ካሉት እጅግ ውድ የሆኑ የከበሩ ድንጋዮች እና የንጉሣዊ ሥርዓቶች አልባሳትን ያካትታል።
በ1979 የኢራን አብዮተኞች ለወራት የንጉሣዊ አገዛዙን በመቃወም አመጽ የተቀላቀለበት ተቃውሞ ካካሄዱ በኋላ የኢራን ንጉሥ አገሩን ጥሎ ተሰደደ።
አያቶላ ኾሜኒ ሥልጣን እስኪጨብጡ ድረስ በተመሰቃቀለው የሥልጣን ሽግግር ወቅት ቅርሶቹ ጠፍተው ይሆናል የሚል ፍርሃት ነግሶ ነበር።
ምንም እንኳን በኋላ ላይ በተካሄደው ቆጠራ ግምጃ ቤቱ ምንም ሳይነካ መቆየቱን ተረጋግጧል።
እዚህ ጥይት በማይበሳቸው መስታወቶች ውስጥ የዳሪያ-ዬ ኑር፣ "ሲ ኦፍ ላይት" የተሰኘው ግዙፍ ሮዝ እንቁ ተቀምጧል።
182 ካራት አካባቢ እንደሆነ የሚገመተው ይህ እንቁ፣ በዓለም ላይ ካሉት ግዙፍ ከሆኑት ሮዝ እንቁዎች አንዱ ነው። ይህም አፈ ታሪኩ ከሕንድ ሞጉል ቤተ መንግሥታት እስከ የፋርስ ነገሥታት ዘውድ አዳራሽ ድረስ ይዘልቃል።
በ1926 የተሠራው እና የጥንታዊ ሳሳኒድ ዘውድ የሆነው በሺዎች በሚቆጠሩ አልማዞች፣ ዕንቁዎች እና ኤመራልዶች የተዋበው የፓህላቪ ዘውድም የሚገኘው እዚሁ ነው።
የብሔራዊ ጌጣጌጥ ግምጃ ቤት የሚገኘው በኢራን ማዕከላዊ ባንክ ውስጥ ነው። ካዝናው እንደ ሙዚየም እና የብሔራዊ ፋይናንስ አምድ ሆኖ ያገለግላል።
ለዘመናት የተሰበሰበው ይህ ቅርስ በ1937 በመንግሥት ባለቤትነት ስር የገባ ሲሆን፣ የኢራንን ገንዘብ ዋጋ ለመደገፍ ረድቷል።
ብዙዎቹ እንቁዎች ልዩ እና የማይተኩ በመሆናቸው የኢራን ብሔራዊ ጌጣጌጥ እውነተኛ ዋጋ ከሚገመተው በላይ እንደሆነ ብዙ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ወደ ተቀመጡበት ስፍራ መግባት የሚቻል ቢሆንም ነገር ግን በጥብቅ የሚጠበቅ ነው።
ጎብኚዎች በኢራን ማዕከላዊ ባንክ ውስጥ ባሉ በርካታ የደኅንነት ፍተሻዎች ውስጥ ማለፍ አለባቸው። እና ስብስቦቹን ለመጎብኘት አስጎብኚ መጠቀም የግድ ሲሆን ስልኮች፣ ቦርሳዎች እና ካሜራዎች የተከለከሉ ናቸው።
የሞና ሊዛ መሰረቅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ያለፈው ሳምንት የፓሪሱ የቅርስ ስርቆት ለሉቨር ሙዚየም የመጀመሪያው አይደለም። ዛሬ በዓለም ላይ በጣም ዝነኛ ሥዕል ተደርጎ የሚቆጠረው የሞና ሊዛ ሥዕል ከመቶ ዓመት በፊት በዘራፊዎች እጅ ገብቶ ነበር።
በአውሮፓውያኑ ሰኞ ነሐሴ 21/1911 ቪንሴንዞ ፔሩጂያ ወደ ሉቨር ገባ። ሙዚየሙ በወቅቱ ዝግ ነበር። እናም የዳ ቪንቺን ዋና ሥራ ይዞ እብስ አለ።
የእሱ ዘረፋ አነስተኛ ዝግጅት የጠየቀ ቢሆንም የፈጠረው ግርግር ግን ግዙፍ ነበር።
ዘረፋው ሲታወቅ ፖሊስ ምርመራ ማድረግ የጀመረ ሲሆን፣ ሉቨርም ለአንድ ሳምንት ተዘግቷል። ሞና ሊዛ ግን ከሁለት ዓመት በላይ ጠፋች።
በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ሥዕሉ የተንጠለጠለበትን ባዶ ቦታ ለማየት ብዙ ሰዎች ወደ ሉቨር ሙዚየም ይጎርፉ ነበር ተብሏል።
በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 10/1913 ፔሩጂያ ሥዕሉን በፍሎረንስ ውስጥ ለነበረው የቅርሳ ቅርሶች ነጋዴ ለአልፍሬዶ ጌሪ ካስተላለፈ በኋላ ተይዟል።
ዘረፋው የተፈጸመው በሙዚየሙ ሠራተኛ ነው ማለት ይቻላል። ጣሊያናዊው ስደተኛ ፔሩጂያ ሥዕሉን የሚከላከለውን የመስታወት በር ከገጠሙት ሰዎች መካከል አንዱ ነው።
የሉቨር ሠራተኞች የሚለብሱት ነጭ ልብስ የነበረው ሲሆን፣ ሥዕሉ በፍሬሙ ላይ እንዴት እንደተሰቀለ ያውቅ ነበር።















