የፈረንሳዩ ሙዚየም በተዘረፈበት ሰዓት የደኅንነት ካሜራው ወደ ሌላ አቅጣጫ ዞሮ እንደነበር ዳይሬክተሯ ተናገሩ

ጭንብል ያደረጉ የፎረንሲክ መርማሪዎች በሙዚየሙ በር ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

88 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የነገሥታት ጌጣጌጦች የተዘረፉበት የፈረንሳዩ ሉቭ ሙዚየም ስርቆቱን በጊዜ ለማስቆም ያልቻለው በተቋሙ ያለው የደኅንነት ካሜራ ደካማ በመሆኑ እንደሆነ የሙዚየሙ ዳይሬክተር ተናገሩ።

ከእሑዱ ዘረፋ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአገሪቱ ሴናተሮች ይፋዊ ማብራሪያ የሰጡት ዳይሬክተሯ ላውረንስ ዴስ ካርስ፤ በሙዚየሙ ቅጥር ውስጥ የሚገኘው የደኅንነት ካሜራ ደካማ እና "ያረጀ" መሆኑን አስረድተዋል።

ዳይሬክተሯ እንደሚናገሩት ዘራፊዎች በገቡበትን የሙዚየሙን ውጫዊ ግድግዳ በኩል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን እንዲሸፍን የተቀመጠው ብቸኛው ካሜራ ወደ ሌላ አቅጣጫ ዞሮ ነበር። በዚህ ምክንያት ዘራፊዎቹ ጌጣጌጦች ወደሚገኝበት 'ጋላሪ ኦፍ አፖሎ' የተባለ ክፍል ሲያመሩ እንዳልቀረጻቸው ገልጸዋል።

"እነዚህን ጌጣጌጦች [ልንጠብቃቸው] አልቻልንም" ያሉት የሙዚየሙ ዳይሬክተር፤ "ሉቭ ሙዚየምም" ሆነ የትኛውም አካል ከእነዚህ "ጨካኝ ወንጀለኞች" ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዳልሆነ አክለዋል።

ስለተፈጸመው ዘረፋ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን እና ቃለ መጠይቆችን ሲሰጡ የቆዩት የፈረንሳይ ሚኒስትሮች ሙዚየሙ የደኅንነት ችግር ያለበት መሆኑን በማስተባበል ሲከራከሩ ቆይተዋል።

ዳይሬክተሯ ዴስ ካርስ ግን ሉቭ ሙዚየም "ተሸንፏል" ሲሉ ተቋሙ ዘራፊዎቹን በጊዜ ሊደርስባቸው አለመቻሉን አምነዋል።

ዴስ ካርስ የሰጡት ይህ ገለጻ፤ በርካታ ጎብኚዎችን በማስተናገድ የዓለማች አንደኛ የሆነው ሙዚየም የደኅንነት ሥርዓት ምን ያህል የተበላሸ እንደሆነ ያሳየ ነው። በአውሮፓውያኑ 2024 ብቻ 8.7 ሚሊዮን ሰዎች ሙዚየሙን ጎብኝተዋል።

ከሙዚየሙ ውጪ ያለው የደኅንነት ካሜራ ሥርዓት "እጅግ አርኪ ያልሆነ" እንደሆነ የሚናገሩት ዳይሬክተሯ፤ አንዳንዶቹ የተቋሙ ሥፍራዎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ለማስተናገድ በማይሆን ደረጃ ያረጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ምንም እንኳን ሙዚየሙ በርካታ ጎብኚዎች የሚጎርፍበት ቢሆንም የደኅንነት ሥርዓቱን ለማሳደግ የሚከናወነው ሥራ መዘግየቱን አንስተዋል። የአገሪቱ ግዙፍ ተቋማት እያጋጠማቸው ያለውን የበጀት እጥረት ጉዳይም አያይዘው ጠቅሰዋል።

በ2021 የሙዚየሙን አስተዳደር የተረከቡት ዳይሬክተሯ ዴስ ካርስ የደኅንነት ካሜራዎችን ብዛት በእጥፍ ማሳደግ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ዳይሬክተሯ እንደሚገልጹት ኃላፊነቱን በተረከቡበት ወቅት የሉቭ የደኅንነት መሣሪያዎች "ጊዜ ያለፈባቸው" እንደሆኑ ተነግሯቸው ነበር።

የዳይሬክተሯን ማብራሪያ ካዳመጡት የአገሪቱ ሴናተሮች መካከል የተወሰኑት የተቋሙ ደኅንነትን በተመለከተ የተነገረውን ለማመን መቸገራቸውን ገልጸዋል።

ዘራፊዎች በገቡበት የሙዚየሙ ውጫዊ ግድግዳ በኩል ለምን አንድ ካሜራ ብቻ ሊኖር እንደቻለ፤ እርሱም ቢሆን ለምን ወደ ሌላ አቅጣጫ ለምን እንደዞረ ጠይቀዋል።

በዚህ ስህተት ምክንያት ዘራፊዎቹን የመጡበት ባለ ሜካኒካል መሰላል ተሽከርካሪ ግለሰቦቹን ጌጣጌጦች ወደሚገኙበት የሕንጻው የመጀመሪያ ወለል ሲያደርስ ሊታይ አልቻለም።

ዳይሬክተሯ፤ "ይህ ሉቭ ውስጥ ያለ ድክመት ነው፤ ሙሉ በሙሉ አምናለሁ" ሲሉ ለሴናተሮች ተናግረዋል።

ዴስ ካርስ ባደረጉት ንግግር፤ ሰዎች ወደ ሙዚየሙ መግባታቸውን እንዳወቁ በፍጥነት ተንቀሳቅሰዋል ያሏቸውን የደኅንነት ጥበቃዎች አመስግነዋል። ነገር ግን "የዘራፊዎቹን መምጣት አስቀድመን አልለየንም... ቅጥራችን ያለበት የጥበቃ ድክመት ታውቆ ነበር" ብለዋል።