በ4 ደቂቃ ውስጥ የ102 ሚሊዮን ዶላር ጌጦችን ከፈረንሳይ ሙዚየም በመስረቅ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በፈረንሳይ ዋና ከተማ ከሚገኘው ሉቨር ሙዚየም እጅግ ውድ የሆኑ ጌጣ ጌጦች ከተዘረፉ ከሳምንት በኋላ ከዝርፊያው ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች መያዛቸውን የፈረንሳይ የመገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።
ለ ፓሪሲያን የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው ሁለቱ ተጠርጣሪ ግለሰቦች የፓሪስ ዳርቻ አካባቢ በሆነችው ሴን-ሴን ዴኒ ነዋሪ ሲሆኑ፣ አንደኛው በቻርልስ ደ ጎል አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ተሳፍሮ ለመጓዝ ሲዘጋጅ ነው በቁጥጥር ስር የዋለው።
በዓለም በበርካታ ሰዎች እንደሚጎበኝ ከሚነገርለት ሙዚየም ውስጥ በተፈጸመው ዘረፋ 102 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ውድ ጌጣጌጦች በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ተሰርቀዋል።
በዋጋ የማይተመኑ ናቸው የተባሉት ውድ ጌጣጌጦች ፓሪስ ውስጥ ከሚገኘው ሙዚየም በመስኮት በኩል ሰብረው በገቡ አራት ግለሰቦች በጠራራ ፀሐይ ተዘርፈው የተወሰዱት የዛሬ ሳምንት እሁድ ነበር።
ከዝርፊያው በኋላ የፈረንሳይ የፍትህ ሚኒስቴር በሙዚየሙ ውስጥ የነበረው የጥበቃ ሥርዓት ዝርፊያውን ለማስቆም ያልቻለ "ውድቀት" እንደገጠመው እና የአገሪቱን "ገጽታ እንዳበላሸው" በይፋ አምኗል።
ዘራፊዎቹ ወደ ሙዚየሙ ሰብረው የገቡት እሁድ ጠዋት ሦስት ሰዓት ተኩል ላይ ሙዚየሙ ለጎብኚዎች ከተከፈተ ከአጭር ጊዜ በኋላ ነው።
በመኪና ላይ የተገጠመ መሰላል ይዘው በመምጣት በአንደኛው የሙዚየሙ መስኮት በኩል ሰብረው በመግባት ነበር ዝርፊያውን የፈጸሙት።
ከአራቱ ዘራፊዎች መካከል ሁለቱ በመሰላሉ በመወጣጣት ወደ ሙዚየሙ መስኮት የደረሱ ሲሆን ከዚያም በመቁረጫ መሳሪያ መስኮቱን በመስበር ወደ ውስጥ መግባት ችለዋል።
ከዚያም ውስጥ የነበሩትን ጠባቂዎች በማስፈራራት እንዲሸሹ ካደረጉ በኋላ ውድ ጌጣጌጦችን ከያዙ የመስታወት ሳጥኖች መካከል ሁለቱን ቆርጠው ለዕይታ የተቀመጡ ውድ ጌጦችን ወስደዋል።
ከዝርፊያው በኋላ የወጣ ቀዳሚ ሪፖርት እንዳመለከተው ዝርፊያው ከተፈጸመባቸው የሙዚየሙ ክፍሎች መካከል አንዱ የደኅንነት ካሜራ እንዳልነበረው የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በሚሊዮኖች ዶላር የሚያወጡትን ጌጣጌጦች ከሙዚየሙ የዘረፉት ሌቦች በሙዚየሙ ውስጥ የቆዩበት ጊዜ አራት ደቂቃ ብቻ ነበር። ከዚያም በገቡበት በመውጣት በትንንሽ ሞተሮች ተፈናጥጠው ከአካባቢው ተሰውረዋል።
መነጋገሪያ ከሆነው ከዚህ ዝርፊያ በኋላ በፈረንሳይ የባሕር ተቋማት አካባቢ ያለው የደኅንነት ጥበቃ እንዲጠብቅ መደረጉን በላሥልጣናት ገልጸዋል።
በሉቨር ሙዚየም የቀሩትን ውድ ጌጦች ደኅንነት ለመጠበቅም ቅርሶቹ ወደ አገሪቱ ብሔራዊ ባንክ ካዝና እንዲዘዋወሩ ተደርጓል።















