ፈረንሳይን ያስደነገጠው ዝርፊያ እንዴት ተፈጸመ?

ዘራፊዎቹ የፓሪሱን ሉቨር ሙዚየም ሰብረው የገቡት ፀሐይ በፓሪስ ሰማይ ላይ ወጥታ ጎብኚዎች ሙዚየሙን ለመጎብኘት መግባት ሲጀምሩ ነበር።
ዘራፊዎቹ በሙዚየሙ ውስጥ ከስምንት ደቂቃዎች በላይ ሳይቆዩ የፈረንሳይ ዋና ከተማ የፓሪስን ጎዳና በፍጥነት አቋርጠው ሲሄዱ አገሪቷ ያሏትን በጣም ውድ ቅርሶችን ይዘው ነበር።
ይህ በቅርብ ካጋጠሙ የዘራፋ ታሪኮች ውስጥ አንዱ የሆነው አስደንጋጩ ዘረፋ የተፈጸመበት መንገድ ታሪክ ነው።
ዘራፊዎቹ እንዴት ሊገቡ ቻሉ?



በ03:30, ከአራቱ ዘራፊዎች ሁለቱ በመኪናው ላይ ያለውን መሰላል ተጠቅመው ድርብ መስኮት ወዳለው በረንዳ መወጣት ጀመሩ።
የመስታወት እና የእንጨት መስኮቶች ዘራፊዎቹ ለያዙት ዘመናዊ መቁረጫ አስቸጋሪ አልነበሩም። የፈረንሳይ ባለሥልጣናት እንዳረጋገጡትም የቅንጡው ቤተ መዘክር መስኮቶች በተገቢው ሁኔታ የተጠናከሩ አልነበሩም።

በ03:34 ዘራፊዎቹ ሙዚየሙ ውስጥ ነበሩ። ፊታቸውን የሸፈኑት ዘራፊዎች ከመቁረጫ መሳሪያቸው ጋር ጥሰው ሲገቡ የጦር መሳሪያ ያልታጠቁት የሙዚየሙ ጠባቂዎች ሸሹ።
በዚህ ጊዜ በዘራፊዎቹ እና በገንዘብ በማይተመኑት ውድ ቅርሶች መካከል የነበረው የተቀመጡበት የመስታወት ሳጥን ነበረ።



ቪዲዮው ከቤተ መዘክሩ ደቡብ ምዕራብ ክፍል ውስጥ የተቀረጸ መሆኑን የቢቢሲ መረጃ ማጣሪያ ለማረጋገጥ ችሏል።
በሙዚየሙ ውስጥ ያለው የደኅንነት ካሜራ ዘራፊዎቹ የፈጀባቸው ጊዜ ከሦስት ደቂቃ ከ57 ሰከንዶች ያልበለጠ መሆኑን እና በዚህ ጊዜ ውስጥም ውድ ጌጦችን ይዘው መሰወራቸውን አንድ የፈረንሳይ ሚኒስትር ተናግረዋል።
ዘራፊዎቹ ፈጣን እና በትክክል ምን ለማድረግ ወደ ሙዚየሙ እንደገቡ ቀድመው የሚያውቁ ናቸው።
የፈረንሣይ ዘውድ ጌጣጌጦች ከ1789 አብዮት በኋላ ሲጠበቁ የነበሩ ቅርሶች ናቸው። በስብስቦቹ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹም ከ19 ኛው ክፍለ ዘመን የመጡ ሲሆን፣ በናፖሊዮን እና በወንድሙ ልጅ ናፖሊዮን ሳልሳዊ ንጉሣዊ ቤተሰቦች ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር።
የጠፉት ቅርሶች
በአጠቃላይ ስምንት ውድ ጌጦች ተሰርቀዋል። የፈረንሣይ ባለሥልጣናት የተዘረፉትን ቅርሶች በዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ ብለዋቸዋል። የከበሩ ድንጋዮች እና ውድ ማዕድናት ካላቸው የገንዘብ ዋጋ ባሻገር አንድ ሚኒስትር ቅርሶቹ 'በሃብት የማይተመን' የቅርስነት ዋጋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

የተሰረቁት ቅርሶች
1-3 ቲያራ፣ የአንገት ጌጥ እና የንግሥት ሆርቴንሴ እና የንግሥት ማሪ-ኤሜሌ የጆሮ ጌጦች
4-5 የእንቁ የአንገት ጌጥ እና ናፖሊዮን ቦናፓርት ለሁለተኛ ሚስቱ ማሪ-ልዊ የሰርግ ስጦታ ያበረከተላት የጆሮ ጌጥ
6-7 የእንቁ እና አልማዝ ቲያራ እንዲሁም የልዕልት ዩጂን የልብስ ጌጥ
8 በልብስ ላይ የሚንጠለጠል ጌጥ
ሁሉ ነገር ዘራፊዎቹ እንዳቀዱት አልነበረም የሄደው፣ የልዕልት ዩጂን ዘውድ ጉዳት ደርሶበት በመተላለፊያ ላይ መገኘቱን እና ወድቆባቸው ሊሆን እንደሚችል ፖሊስ አረጋግጧል።

የፈረንሣይ ዐቃቤ ሕግ ሁለቱ ዘራፊዎች በፖሊስ ምርመራ እየተደረገባቸው ያሉ ጃኬቶችን ጨምሮ አንዳንድ ነገሮችን ትተው መሄዳቸውን ገልጿል።
በ 03:35, ላይ በአፖሎ ቤተ መዘክር ውስጥ አንድ ነገር መከሰቱን በተመለከተ በሙዚየሙ ሠራተኞች መካከል መወራት ጀመረ። በመቆጣጠሪ ክፍሉ ውስጥ የማስጠንቀቂያ ደውል የተሰማ ቢሆንም፣ ነገር ግን ምን ያህል በስፋት ስለመሰማቱ የታወቀ ነገር የለም። ፖሊስ በአሁኑ ወቅት የማስጠንቀቂያ ደወሉ በትክክል እየሠራ እንደነበረ ለማወቅ ምርመራ እያደረገ ነው።
አንድ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ እንደገለጸው የሙዚየሙ ጠባቂዎች ጎብኚዎችን ከአፖሎ ቤተ መዘክር ሲየስወጡ እና ሌሎች ደግሞ ወደ ሙዚየሙ በብዛት ሲሄዱ ተመልክቷል።
መጀመሪያ ላይ ጎብኚዎች ወደ ሌላ የሙዚየሙ ክፍል እንዲሄዱ ቢደረግም፤ ጠባቂዎቹ በሬዲዮ ሌላ መልዕክት ሲመጣላቸው ደግሞ "ሁኔታው ተለወጠ" ብሏል።
በ03፡38 ላይ ሙዚየሙን ለቅቀው ከመውጣታቸው በፊት, ዘራፊዎቹ የተጠቀሙበትን በመኪና ላይ የተገጠመ መሰላል በእሳት ለማቃጠል ሞክረው ነበር። ከዚያም በፓሪስ ጠብብ መንገዶች ላይ በመሽሎክሎክ በሰዓት 100 ኪሜ መጓዝ በምትችል ትንሽዬ ሞተር ሳይክል አምልጠዋል።

መርማሪዎች ዘራፊዎቹ ከፓሪስ ከተማ ለመውጣት የሚያስችላቸው አውራ ጎዳና ወደ ሚገኝበት ደቡባዊ አቅጣጫ ማቅናታቸውን ያምናሉ።
ለአሁን ዘራፊዎቹ ሸሽተው የሄዱበት ቦታ እንቆቅልሽ ሆኗል። እናም ዘራፊዎቹ ያሉበትን ቦታ ማወቅ የዘረፏቸውን ጌጣጌጦች ያህል ለፈረንሳይ ፖሊስ ዋጋ አለው።
ተጨማሪ ዘገባ፡ ሾን ሴዶን፣ ሪቻርድ ኧርቪን-ብራውን እና ፖል ኪርቢ
ምሥሎች
ሉቨር ሙዚየም፣ አርኤምኤን - ግራንድ ፓላይስ፣ ቢኤፍኤምቲቪ፣ ጌቲ ኢሜጅስ







