የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታዮች ለማግኘት ልጇን የመረዘችው ተጽዕኖ ፈጣሪ ተከሰሰች

አውስትራሊያዊቷ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ

የፎቶው ባለመብት, Queensland Police

አውስትራሊያዊቷ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ተከታዮች ለማግኘትና እርዳታ ለማሰባሰብ በሚል ልጇን በመመረዟ ክስ ቀረረበባት።

አውስትራሊያ ኩዊንስላንድ የምትኖረው እናት ልጇ ስላለባት ሕመም በማኅበራዊ ሚዲያ በመናገር ትታወቃለች።

መርማሪዎች እንዳሉት ግን የአንድ ዓመት ልጇን እየመረዘቻት ነበር። ልጇ "ከፍተኛ ሕመምና ጭንቀት ውስጥ" ስትሆን ይህን በመቅረጽ በማኅበራዊ ሚዲያ ታቀርበዋለች።

ለወራት ምርመራ ከተካሄደ በኋላ የ34 ዓመቷ ሴት በቁጥጥር ሥር ውላለች። በማሰቃየት፣ መርዝ በመስጠት፣ ልጅን በመበዝበዝና በማጭበርበር ተከሳለች።

የፖሊስ ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር ፖል ዳልተን "ድርጊቱ እንዴት አሰቃቂና አስቀያሚ እንደሆነ ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል" ብለዋል።

ከነሐሴ እስከ ጥቅምት ድረስ ለልጇ የተለያዩ በሐኪም ያልታዘዙ መድኃኒቶችን እየሰጠች እንደነበር ታውቋል።

ፈቃድ ያልተሰጣቸው መድኃኒቶችን መግዛቷን ለመሸፋፈን ሞክራለች ተብሏል።

ሌሎች ሰዎች ወስደዋቸው የተረፉ መድኃኒቶችን በመውሰድም ለልጇ ሰጥታለች።

ፖሊስ ምርመራውን ጥቅምት ላይ ነበር የጀመረው። ልጅቷ ታማ ሆስፒታል ከሄደች በኋላ ምርመራ ተከፍቷል።

ልጅቷ "ከፍተኛ ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ጉዳት" እንደደረሰባት ተገልጿል።

ለልጅቷ በተደረገው ምርመራ ያልታዘዙ መድኃኒቶችን እየወሰደች እንደነበር ታውቋል።

ተከሳሿ ወደ 37 ሺህ ዶላር ገደማ በጎፈንድሚ አሰባስባለች።

እርዳታ ማሰባሰቢያው ድረ ገጽ ገንዘቡን እንደሚመልስ ፖሊስ አስታውቋል።

ፖሊስ እንዳለው በዚህ ብዝበዛ ውስጥ ተሳትፈው ከሆነ በሌሎችም ላይ ምርመራ ቢያደርግም የተሳተፈ ሰው አላገኘም።

ተከሳሿ በቅርቡ ፍርድ ቤት ትቀርባለች።