በሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን በጎሳ ግጭት ምክንያት የሰዎች ሕይወት አለፈ

በሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን ዋርዴር ወረዳ በሁለት ንዑስ ጎሳዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰዎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ ባለሥልጣን እና የሰብዓዊ መብት ባለሙያ ለቢቢሲ ተናገሩ።
በክልሉ የሚነቀሳቀሰው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ትላንት ማክሰኞ ሰኔ 25/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ “በሁለት ወንድማማች ንዑስ ጎሳዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት የሰው ሕይወት ጠፍተል” ብሏል።
የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲቃድር ረሺድ በበኩላቸው “የተከሰተው ግጭት የሦስት ሰዎች ሕይወት ያለፈበት ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት ተከሰተ በተባለው ግጭት አራት ሰዎች መሞታቸውን የገለጹት ደግሞ በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ኦርጋናይዜሽን ኦፍ ቪክቲምስ ኤንድ ሰርቫይቨርስ የተባለ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አህመድ መሐመድ ናቸው።
የሟቾችን ቁጥር በተመለከተ የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ “እኔ ያለኝ መረጃ ሦስት ሰዎች እንደሞቱ ነው፤ አንድ ቁስለኛ ሞቶ አራት ሊሆኑ ይችላሉ” ሲሉ ስለደረሰው ጉዳት ተናግረዋል።
በሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን ግጭት ሲከሰት ይህ የመጀመሪያው አለመሆኑን የክልሉ ባለሥልጣን እና አቶ አህመድ ይገልጻሉ።
አቶ አህመድ ከአንድ ዓመት በፊት ሰኔ/2015 ዓ.ም. በመሬት ይገባኛል ምክንያት ግጭት መፈጠሩን ያስታወሳሉ።
በሶማሌ ክልል ለተጎጂዎች ለሚሟገተው ተቋም የሚሠሩት አቶ አህመድ፤ ግጭቶቹ የሚከሰቱት ‘መካሂል’ በተሰኘ ጎሳ ስር በሚገኙ ‘ኢብራሂም’ እና ‘ኢስማኤል’ በተሰኙ ንዑስ ጎሳዎች መካከል መሆኑን አስረድተዋል።
ባለፈው ዓመት አጋጥሞ በነበረው ግጭት ከኢስማኤል ንዑስ ጎሳ የሆኑ አምስት ሰዎችን መግደላቸውን አቶ አህመድ ያስታውሳሉ።
በተመሳሳይ በዚህ ዓመት ሚያዝያ መጀመሪያ ላይ በኢስማኤል አባላት ጋሮንቃ የምትባል ቀበሌ በተከፈተ ተኩስ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን አቶ አህመድ ጨምረው ይናገራሉ።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተከሰተው ግጭት ደግሞ አራት ሰዎች ከ‘ኢስማኤል’ ጎሳ መገደላቸውን ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, SDM
የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው “እኔ እንደ መንግሥት አመራር ጥቃት ፈጻሚው ይሄ ጎሳ ነው ብሎ መጥራት አግባብ አይመስለኝም” ካሉ በኋላ፣ በግጭቶቹ ተሳተፊ ሆኑትን የንዑስ ጎሳዎችን ስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።
ነገር ግን በአካባቢው ተደጋጋሚ ግጭቶች እንደሚከሰቱ አረጋግጠው፤ “መንስኤው በመንደር ማሰባሰብ ዙሪያ የመሬት የይገባኛል ጥያቄ ስለሆነ የጎሳው መሬት ይገባኛል፣ እኔ ነኝ እዚህ ምኖረው፣ የእኔ ነበር የሚል ግጭት ስለሆነ ታሪኩም ስለሚታወቅ [ችግሩ] ይፈታል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኦብነግ በመግለጫው ላይ፤ በሶማሌ ክልል የሚገኙ “የአገር ሽማግሌዎች በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገቡ እና ግጭት ውስጥ በገቡት ወገኖች መካከል ያለውን አለመግባባት እንዲፈቱ” ጠይቋል።
በተጨማሪም፤ የሶማሌ ክልል መንግሥት “አፋጣኝ እና ቆራጥ እርምጃ እንዲወስድ” አሳስቧል።
አቶ አብዲቃድር ረሺድ ከግጭት በኋላ “የፀጥታ ኃይሎች በአካባቢው ደርሰው ችግሩን ተቆጣጥረውታል፤ የሀገር ሽማግሌዎችም እየተነጋገሩ ይገኛሉ” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።












