ባይደን ለእስራኤል ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የጦር መሣሪያ ድጋፍ ለማድረግ ወሰኑ

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዋይት ሐውስ፤ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የጦር መሣሪያ ለእስራኤል ለመለገስ ማቀዱን ለሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አሳውቋል።

ምንም እንኳ እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ የምትገኘው ራፋህ ላይ ልታደርግ ያሰበችውን ወታደራዊ እርምጃ አሜሪካ ብትቃወምም ድጋፉን ለማድረግ ግን አስባለች።

ዋይት ሐውስ ባለፈው ሳምንት ለእስራኤል ሊልካቸው ያሰባቸውን ቦምቦች ለጊዜው የገታው ቦምቦቹ በርካታ ሰዎች በተሰበሰቡበት ከተጣሉ ሰላማዊ ዜጎች ይገደላሉ በሚል ስጋት ነው።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደገለጡት አዲስ ዕቅድ በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት [ኮንግረስ] መፅደቅ አለበት።

700 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ታንኮች፤ 500 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ለታክቲካዊ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም 60 ሚሊዮን ለሞርታር የታሰበ ነው ሲል አሶሺየትድ ፕረስ የተሰኘው የዜና ወኪል ዘግቧል።

ማክሰኞ ዕለት የእስራኤል ታንኮች ወደ ደቡብ ምስራቅ ጋዛ ተጉዘው መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ታይተዋል።

ባለፈው ወር የአሜሪካ ኮንግረስ ለእስራኤል፣ ዩክሬን እና ታይዋን የሚሆን 95 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማፅደቁ ይታወሳል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለፈው ሳምንት ያወጣው መግለጫ ለእስራኤል የተሰጡ አሜሪካ ሠራሽ የጦር መሣሪያዎች ዓለም አቀፍ ሕግ በሚጥስ መልኩ ጥቅም ላይ ሳይውሉ አልቀረም ይላል።

ምንም እንኳ መግለጫው እስራኤል በጋዛ እያደረገች ያለችውን እርምጃ ቢቃወምም የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ዓለም አቀፍ ሕግ ጥሷል ከማለት ተቆጥቧል።

አክሎም እስራኤል የአሜሪካ የጦር መሣሪያዎችን በሕጋዊ መንገድ ለመጠቀም የገባችው ቃል "እውነተኛ እና አስተማማኝ ነው" ብሏል።

ባይደን ባለፈው ሳምንት ወደ እስራኤል የሚደረግ የጦር መሣሪያ ዝውውር እንዲቆም ባለፈው ሳምንት ካወጁ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የ1 ቢሊዮን እርዳታ ለማድረግ ያቀዱት።

ፕሬዝደንት 900 ኪሎ ግራም የሚመዝን ቦምብ ወደ እስራኤል እንዳይላክ ያገዱት በምድር ጦር ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ በሚል ነው።

ጊዜያዊ እገዳው ለምን ተብለው በሲኤንኤን የተጠየቁት ባይደን "በእነዚህ ቦምቦች ምክንያት ሰላማዊ ሰዎች ዜጎች ተገድለዋል" ሲሉ መልሰዋል።

ለእስራኤል የሚደረግ የጦር መሣሪያ ድጋፍ በሚቀጥለው ኅዳር ምርጫ ፓርቲያቸውን ወክለው ለሚወዳደሩት ባይደን ዕዳ እንዳይሆንባቸው ተሰግቷል።

በኮንግረስ የሚገኙ ሪፐብሊካኖች ከዚህ በኋላ የጦር መሣሪያ እርዳታው እንዳይታገድ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ አውጥተዋል።

በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7 ሐማስ እስራኤል ላይ ጥቃት ሰንዝሮ 1200 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ነው እስራኤል ቡድኑን ለማጥፋት በጋዛ ጦርነት የከፈተችው።

በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንደሚለው በጋዛ እስካሁን 25170 ሰዎች ተገድለዋል።