ኢራን የኒውክሌር ቦምብ መገንባት 'ባያቅተኝም ፍላጎቱ የለኝም' ማለቷ ተዘገበ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኢራን አውቶሚክ ኃይል ኃላፊ መሐመድ ኢስላሚ አገራቸው የኒውክሌር የጦር መሣሪያ የመገንባት አቅም ቢኖራትም ይህንን መሣሪያ የመገንባት ዕቅድ ግን እንደሌላት ተናገሩ።
የኢራን የዜና ተቋም ኃላፊውን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ኢራን የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ለመሥራት የሚያስችል አቅም አላት።
ከዚህ ቀደም ሌላ የኢራን ከፍተኛ አመራርም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።
የኢራን አመራሮች በግልጽ ስለ ኒውክሌር ቦምብ ሲናገሩ እምብዛም አይደመጡም ነበር። አሁን ግን በአደባባይ የሚሰጧቸው አስተያየቶች የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም በርካቶችን እንዲያሰጋ ምክንያት ሆኗል።
የኢራን የኒውክሌር አጠቃቀም የሚገድበው ስምምነት ውድቅ ከሆነ በኋላ በዘርፉ የምታደርገው እንቅስቃሴ እያደገ መምጣቱ ተሰምቷል።
እአአ በ2015 የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊነት ጥያቄ ውስጥ መግባት የጀመረው በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምክንያት አሜሪካ ስምምነቱን ጥላ ከወጣች በኋላ ነው።
አሜሪካ ኢራንን የሚያሽመደምዱ የምጣኔ ሀብት ማዕቀቦች ጥላለች።
ኢራን ኒውክሌርን ለሰላማዊ አላማ እንደምታውል ብትገልጽም ምዕራባውያን አገራት አያምኗትም።
ኢራን ኒውክሌርን በማበልጸግ ዓለም ሊቆጣጠረው የማይችለው ደረጃ ከመድረሷ በፊት ስምምነቱ እንዲታደስ ምዕራባውያን እየጣሩ ነው።
የኢራን አውቶሚክ ኃይል ኃላፊ መሐመድ ኢስላሚ፣ በከፊል የመንግሥት ከሆነው ፋርስ የዜና ተቋም ጋር ባደሩት ቆይታ፣ “ኢራን አውቶሚክ ቦንብ ለመሥራት የቴክኒክ ብቃቱ አላት። ነገር ግን መሣሪያ መሥራት አጀንዳችን አይደለም” ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ካሚል ካርዚ የተባሉ የኢራን ከፍተኛ አመራር የሰጡትን አስተያየት ኃላፊው አረጋግጠዋል።
ካሚል ካርዚ “ኢራን ኒውክሌር ቦንብ ለመሥራት የቴክኒክ ብቃቱ አላት። ነገር ግን መሣሪያ ለመሥራት አልወሰነችም” ሲሉ ለአል ጀዚራ ገልጸው ነበር።
ኢራን በከፍተኛ የሆነ ዩራኒየም አበልጽጋ ኒውክሌር የጦር መሣሪያ መሥራት የምትችልበት ጊዜ ብዙዎችን እያሳሰበ ይገኛል።
የዓለም አቀፉ አውቶሚክ ኃይል ተቋም ሊቀ መንበር ራፋኤል ግሮሲ ሰኔ ወር ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢራን በሳምንታት ውስጥ መሣሪያ መሥራት የሚያስችላት የበለጸገ ዩራኒየም ማግኘት እንምትችል ጠቁመዋል።
የኒውክሌር ስምምነቱ ሳይፈርስ በፊት፣ ኢራን መሣሪያ ለመሥራት የሚያስፈልጋት ጊዜ አንድ ዓመት እንደሆነ አሜሪካ ገምታ ነበር።
ራፋኤል ግሮሲ እንደሚሉት፣ ኢራን መሣሪያ ለመሥራት የሚያስፈልጓትን ግብዓቶች ማብላላት ትችላለች ማለት ኒውክሌር ቦንብ ማምረት ትችላለች ማለት አይደለም።
የሚመሩት ተቋም ባወጣው አሐዝ መሠረት፣ ኢራን 43.1 ኪሎ ግራም የሚመዝን በ60 በመቶ የተጣራ የዩራንየም ክምችት አላት።
የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ለመሥራት የሚያስፈልገው በ90 በመቶ የተጣራ 25 ኪሎ ግራም ዩራኒየም ነው።
የ2015ቱን የኒውክሌር ስምምነት ለማደስ ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት ነው ኢራን የኒውክሌር የጦር መሣሪያ የመሥራት “የቴክኒክ ብቃቱ አለኝ” ያለችው።
ባለፈው ሰኔ ላይ ኳታር ውስጥ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ስምምነቱን ለማደስ ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ቢሞከርም ስኬታማ አልሆነም።












