በአፍጋኒስታን እና ኢራን መካከል የድንበር ግጭት ተቀስቅሶ አንድ ሰው ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአፍጋኒስታኑ የታሊባን ጦር እና የኢራን ድንበር ጠባቂዎች ተጋጭተው አንድ ወታደር መገደሉ ተዘገበ።
ትናንት እሁድ ሐምሌ 24/2014 ዓ.ም. በአፍጋኒስታኗ ኒምሮዝ ግዛት እና በኢራኗ ሂርማንድ ግዛት አዋሳኝ የድንበር አካባቢ በተካሄደው ጦርነት አንድ ወታደሩ መገደሉን ታሊባን ገልጿል።
አገራቱ ለችግሩ መቀስቀስ አንዳቸው ሌላኛውን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
ከዓመት በፊት የታሊባን ታጣቂዎች አፍጋኒስታንን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ በአገራቱ ድንበር ላይ በርካታ ግጭቶች ተከስተዋል።
የሰሞኑ ግጭት ትክክለኛ ምክንያት ግልጽ አይደለም።
የኒምሮዝ ፖሊስ ቃል አቀባይ ባህራም ሃቅማል ለሮይተርስ የዜና ወኪል “አንድ ወታደር ተገድሎብናል ሌላ አንድ ደግሞ ቆስሎብናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ባራዛንዴህ ፋርስ የዜና ወኪል በኢራን ሲስታን ቫ ባሉቼስታን ግዛት የሂርማንድ ባለሥልጣን የሆኑትን ማይሳም ባራዛንዲህን ጠቅሶ እንደዘገበው በኢራን በኩል ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰም።
የኢራን ታስኒም የዜና ወኪል በበኩሉ ጦርነቱ የተቀሰቀሰው የታሊባን ጦር “የአፍጋኒስታን ግዛት ባልሆነ አካባቢ” ባንዲራውን ለመስቀል ለማድረግ በመሞከሩ ነው ብሏል።
“ለበርካታ ደቂቃዎች የቆየ የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል” ሲልም አክሏል።
“የእኛ ኃይሎች አስፈላጊውን ምላሽ ሰጥተዋል” ብለዋል ባራዛንዲህ።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ወር በተመሳሳይ በአካባቢው በተከሰተ ግጭት የኢራን ድንበር ጠባቂ አባለ መገደሉን ገልጾ ነበር።












