ዩክሬን አሉኝ የምትላቸው ባለሀብት በሩሲያ ጥቃት ተገደሉ

ባለሃብቱ ኦሌክሲ ቫዳቱርስኪ ሃብታቸው 450 ሚሊዮን ዶላር ይገመት ነበር

የፎቶው ባለመብት, NIBULON

ዩክሬን አሉኝ ከምትላቸው ሀብታም ነጋዴዎች መካከል አንዱ የነበሩት ኦሌክሲ ቫዳቱርስኪ ከባለቤታቸው ጋር በደቡባዊ ዩክሬን ሚኮላይቭ ከተማ በሩሲያ በተፈፀመ የሚሳኤል ጠቃት ተገደሉ።

የ74 ዓመቱ ቫዳቱርስኪ እና ባለቤታቸው ራይሳ የሩሲያ ሚሳኤል መኖሪያ ቤታቸውን ከመታ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ቫዳቱርስኪ በእህል ንግድ የተሰማራ ኒቡሌን የተባለ ግዙፉ ኩባንያ ባለቤት ነበሩ። እኚህ ባለሃብት በቅርቡ 'የዩክሬን ጀግና' ክብርን አግኝተው ነበር።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ የባለሃብቱን ሕልፈት ትልቅ ጉዳት ሲሉ ገልፀውታል።

የሚኮላይቭ ከተማ ከንቲባ ኦሌክሳንደር ሴንኬቪች ባለሃብቱ በተገደሉበት ዕለት የተፈጸመው ጥቃት ምናልባት እስካሁን በከተማዋ ላይ የደረሰው ከባዱ የሩሲያ ጥቃት ሳይሆን አይቀርም ብለዋል።

የሩሲያ ጦር በከተማዋ በሚገኙ ሆቴል፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከል፣ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት አድርሷል።

ሚኮላይቭ ከተማ በጥቁር ባሕር ላይ ወደሚገኘው የዩክሬን ትልቁ ወደብ ኦዴሳ በሚወስደው ዋና መንገድ ላይ የምትገኝ ከተማ ስትሆን፤ ሩሲያ ወረራዋን በየካቲት 24 ከጀመረች በኋላ በተደጋጋሚ ጥቃት ያስተናገደች ከተማ ነች።

የፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ አማካሪ ሩሲያ ነጋዴውን ሆን ብላ ኢላማ አድርጋለች ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ማይካሂሎ ፖዶሊያክ እንደሚሉት ከተተኮሱት ሚሳኤሎች አንዱ የነጋዴውን መኝታ ክፍል መምታቱ ጥቃቱ ሆነ ተብሎ ነጋዴው ላይ ማነጣጠሩ "አያጠራጥርም" ብለዋል።

ሟቹ ባለሃብት በባለቤትነት የሚመሩት ኒቡሎን የዩክሬንን የእህል ምርት ወደ ውጭ ለመላክ የሚረዱ የማከማቻ ቦታዎችን እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ገንብቷል።

ዩክሬን እና ሩሲያ የስንዴ እና ሌሎች እህሎች ለዓለም የሚያቀርቡ ቀዳሚ አገራት ሲሆኑ በጦርነቱ ምክንያት ወደ ውጭ የሚላኩ የእህል ምርቶች መስተጓጎል በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋጋ ጭማሪን አስከትሏል።

ሁለቱ አገራት የምግብ ቀውሱን ለመቅረፍ ያለመ ስምምነት ባለፈው ሳምንት በቱርክ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አደራዳሪነት ተፈራርመዋል።

ነገር ግን ሩሲያ በኦዴሳ ወደብ ላይ ባደረሰችው ጥቃት ስምምነቱ ይስተጓጎል ይሆን የሚሉ ስጋቶች አይለዋል።