የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር በአውሮፕላናቸው የቴክኒክ ብልሽት ምክንያት ህንድ ለመቆየት ተገደዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ አውሮፕላናቸው የቴክኒክ ብልሽት ገጥሞት ያለዕቅዳቸው ሕንድ ለመቆየት ተገደዋል።
የካናዳ ጦር ሠራዊት ትሩዶን በፍጥነት ወደ ቤታቸው ሊያመጣቸው እየተሯሯጠ ቢሆንም ከማክሰኞ ከሰዓት በፊት ካናዳ እንደማይገቡ ቢሯቸው ገልጧል።
በቡድን 20 ሃገራት ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ ሕንድ ያቀኑት ትሩዶ ከሕንዱ አቻቸው ናሬንድራ ሞዲ ጋር ጠጠር ያለ ውይይት ካደረጉ በኋላ ዕለተ ሰንበት ነበር ሊመለሱ ያቀዱት።
ቢሯቸው እንደገለጠው በረራቸው “ይህ ነው የሚባል ጊዜ አልተቆረጠለትም።”
የካናዳ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት ለቢቢሲ በላከው መግለጫ “የካናዳ ሮያል አየር ኃይል ሲሲ-150 ፖላሪስ የተሰኘችው አውሮፕላን «የቴክኒክ ብልሽት» ገጥሟታል” ብሏል።
መግለጫው አክሎ “የተሳፋሪዎቻችንን ደኅንነት መጠበቅ የኛ ኃላፊነት ነው፤ ለዚህም ነው ከበረራ በፊት ሁሌም የቴክኒክ ምርመራ የምናካሂደው” ብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶን ይዛ ከሕንድ የምትመለስ ምትክ አውሮፕላን ማክሰኞ ከዩናይትድ ኪንግደም ተነስታ እንደምትሄድ ተሰምቷል።
ነገር ግን የካናዳ መከላካይ ሠራዊት ምትክ አውሮፕላን መዘጋጀቱን ከመጥቀስ ውጭ የአውሮፕላኗ መነሻ ከየት? መቸስ ይመለሳሉ? የሚሉ ጥያቄዎችን ከመመለስ ተቆጥቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ በተራዘመ በረራ ሲንገላቱ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።
በአውሮፓውያኑ 2019 ጋዜጠኞችን አሳፍራ የነበረች አውሮፕላን እሳቸውን ይዛ ልትበር ከቆመች ሌላ አውሮፕላን ክንፍ ጋር መጋጨቷ የሚታወስ ነው።
በካናዳዋ ብሪቲሽ ኮለምቢያ ባለፈው ሰኔ የሲክ ብሔር መገንጠልን የሚያቀነቅነው ሲንግ ኒጃር መገደሉ ይታወሳል።
የሲክ መገንጠልን የሚያቀነቅኑ ሰዎች በቶሮንቶ አውራ ጎዳና የሕንድ መንግሥትን በይፋ ተቃውመዋል። ለግለሰቡ መገደሉም ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል ብለዋል።
ሞዲ ከትሩዶ በነበራቸው ውይይት “ፀረ-ሕንድ አክቲቪስቶች በካናዳ እየበረከቱ በመሆናቸው” የተሰማቸውን ስጋት ገልጠዋል።












