ክብርት ሳሕለወርቅ በሥራ ጉዳይ ‘ወታደራዊ ዲሲፕሊን’ ነው ያላቸው - የፕሬዝዳንቷ የቀድሞ የግል ፎቶግራፈር

የፎቶው ባለመብት, Addis
* ይህ ፅሑፍ በድጋሚ የታተመ ነው
ፎቶግራፈርነት በዘር ይወረሳል?
አዲስ አእምሮ ጋ የደረሰው እንደዚያ ይመስላል።
በድሮ ጊዜ አያቷ ፎቶግራፈር ነበሩ። የአያቷ 9 ልጆች ሁሉም ፎቶ አንሺ ነበሩ፤ ወይም ናቸው።
ከዘጠኙ የአያቷ ልጆች አንዷ እናቷ ናቸው።
እናት የፎቶ ሙያን ከአባት ተቀብለው ለልጃቸው አሻገሩ። የካሜራ ቅብብሎሹ አሁን አዲስ አእምሮ ዘንድ ደርሷል። 3ኛ ትውልድ።
እስኪ አያቷን ተዋወቋቸው። አቶ ሰፊው ተበጀ ይባላሉ።
የወልድያ ሕዝብ ‘ጉርድ ፎቶ’ የተነሳው በርሳቸው ካሜራ ነው። የመጀመርያው ፎቶ ቤትም የርሳቸው ሳይሆን አይቀርም። ‘ፎቶ አይጠገብን’ ማን አያውቀውምና?
ብቻ የአቶ ሰፊው ታሪክ ሰፊ ነው። በዚያ ላይ ረዥም ነው፤ እንደ ዕድሜያቸው። አሁን ከ90 ደፍነዋል። የርሳቸው ታሪክና ሙያ ዘለግ ያለ ስለሆነ ለሌላ ጊዜ እናሳድረው።
ከጀመርነው አንዘልቀውማ። በጃንሆይ ጊዜ ሥራ ጀምረው፣ የደርግ ባለሥልጣናትን በጥንቱ በጠዋቱ የ’ያሺካ ካሜራ’ ፎቶ ቀጭ ያደረጉ ሰው ናቸው። ብቻ የርሳቸው ታሪክ ይደር።
ወደ የልጅ ልጅ እንምጣ። ወደ አዲስ አእምሮ።
በመሀል ግን እናት አሉ፤ ወ/ሮ ሰርካለም ሰፊው። ስለርሳቸው አንድ ሁለት መስመር?
ወ/ሮ ሰርካለም የአዲስ አእምሮ እናት ናቸው።
ደርግ ሲወድቅ ከወልድያ አዲስ አበባ መጥተው አራት ኪሎ ዕውቅ ፎቶ ቤት ከፈቱ። አዲስና እህቶቿ ደግሞ ፊልም አጣቢ ሆነው ‘ዳርክ ሩም’ ውስጥ አደጉ። ሕይወታቸው ግን ብርሃናማ ነበር።
አዲስ ከ’ዳርክ ሩም’ ወጥታ ብዙ ተማረች። ተምራ፣ አድጋ፣ ዩኒቨርስቲ ገብታ፣ የእርሻ አኮኖሚክስ ዲግሪ ጭና፣ ኤልፎራ ሠርታ፣ ዞራ- ዞራ- ዞራ ከቤተሰቡ ሙያ አልወጣችም። ዕጣ ፈንታ ይሆን?
በመጨረሻ የ4ኪሎው የእናቷ ፎቶ ቤት፣ ወደ 4ኪሎ ቤተ መንግሥት አስጠጋት። የዕጣ ፈንታ ነገር።
አንዳንዱን ታሪክ አዲስ ራሷ ብትተርከው ይሻላል።

የፎቶው ባለመብት, Addis
‘ዐቢይ አሕመድ ኖቤል ያሸነፉ ጊዜ...’
“አባቴ ካህን ነው። ቅድስተ ሥላሴ ያገለግላል። እናቴ ደግሞ ከመንፈሳዊ ኮሌጅ ለምርቃት ፎቶ ታነሳ ነበር። አራት ኪሎና ግንፍሌ አካባቢ “ቅድስት ሥላሴ ፎቶ ቤት” ማንም ያውቀዋል።
እናቴ በፊልም ዘመን ነው ብዙ የሠራችው። እኔ በዲጂታሉ ማገዝ ነበረብኝ።
ልጅ እያለሁ የማስታውሰው አሁን ‘ፎቶሾፕ’ የሚባለው ነገር እሷ ‘እጅ ሥራ’ የምትለው ነው። በእርሳስ ነበር የሚሠራው።
እናቴ የሆነ ሳጥን አላት፤ እና እሱ ላይ ሆና እጅ ሥራ ስትሠራ ዐይኗን ሲያማት ትዝ ይለኛል። እኔ በእርሳሱ ስጫወት ትዝ ይለኛል።
‘የሕይወት እውነተኛ ዓላማችሁ ሕጻን እያላችሁ የምትመኙት ነው’ ይባላል። ‘የልጅነታችን ድብቆ አእምሮ ‘Subconscious Inner Child’ አብሮን አለ፤ ብናድግም አይጠፋም።
እና ተመልሼ ሳስበው፣ ሕጻን እያለሁ ጊቢ ውስጥ በማስታጠቢያ ውሃ አድርጌ መዘፍዘያው ውስጥ ልክ እንደ ፎቶ ወረቀቶችን ሳገላብጥ ትዝ ይለኛል።
የሆነ ሰዓት እኔም ፎቶግራፈር እንደምሆን ‘deep down’ አውቅ ነበር።
አድጌ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ ደረሰኝ። ቤተሰብ ዲግሪ እንዲኖረኝ ስለሚጠብቅ መማር ነበረብኝ። ተምሬ ተመረቅኩኝ።
ከተመረቅኩ በኋላ ለሦስት ዓመት ሚድሮክ፣ ኤልፎራ ሠራሁ። ተቀጥሬ እየሠራሁ ግን ልቤ አላረፈም። ነፍሴ ትቅበዘበዝ ነበር። ስለዚህ 11፡00 ሰዓት ከሥራ ከወጣሁ በኋላ ወደተለያዩ ሥልጠናዎች እሄድ ነበር።
በኋላ ‘ጎተ ኢንስቲትዩት’ ፎቶ የማንሳት ሥልጠና አገኘሁ። በምሳ ሰዓት ሹልክ ብዬ እየወጣሁ ሥልጠና ጨረስኩ።
ወርክሾፑን የሚሰጠው አንጋፋው ፎቶግራፈር ሚካኤል ፀጋዬ ነበር። ራሴን ሳስተዋውቅ ‘አያቴም ፎቶግራፈር ነበር። እናቴም ፎቶግራፈር ነበረች’ ብዬ ተናገርኩ፤ ተገረመ።
ፕሮጀክት ተሰጠኝ። የመጀመሪያው የፎቶግራፊ ፕሮጀክቴ አያቴን ፎቶ ማንሳት ሆነ።
የምሠራበት ቦታ ብዙም የሥራ ጫና ስላልነበረ 15 ቀን ፈቃድ ወስጄ፣ የመጀመሪያ ካሜራዬን ይዤ፤ ወልድያ አያቴ ጋር ሄጄ ቃለ ምልልስ አደረግኩለት።
ሌላ ጊዜ አያቴ ጋር ስሄድ ከነበረው የተለየ ግንኙነት ፈጥሬ ተመለስኩ። ፎቶ ሳነሳው፣ እሱ ድሮ ሲሠራው የነበረውን ነገር ስሠራ መደነቁ አልቀረም።
ቃለ ምልልስ ሳደርግለት ደስ አለው። ምክንያቱም ወደኋላ መለስኩት። ‘እንዴት ነው የተነሳኸው? ምን ዓይነት ካሜራ ነበረህ? ፊልሞቹን አሳየኝ እስኪ?’ ስለው ተገረመ። የድሮውን ባለ ሁለት ሌንስ ‘ያሺካ’ ካሜራ አሳየኝ።

የፎቶው ባለመብት, Addis
‘አያቴ ፎቶ ሲያነሳ ሰላይ ይመስላቸው ነበር’
አያቴ ድሮ ፎቶ ሲያነሳ ሰላይ ይባል ነበር። ‘ለመንግሥት ልትሰልል ነው አይደል?’ ይሉት ነበር።
የሱ ካሜራው የሚጎርሰው 12 ፊልም ነበር። 12 ፊልም ብቻ ደግሞ አያዋጣውም። ስለዚህ አንዷ ፊልም ላይ አራት ሰዎችን ይደረድርና አራቱንም ያነሳል። እና ዲቨሎፕ ሲያደርገው ቆርጦ ነጣጥሎ አራቱን ሰዎች ያወጣቸዋል።
ከአራቱ አንዱ ዐይኑን ከጨፈነ በጣም ይበሳጭ ነበር። (ሳቅ) ምክንያቱም የአንዱ መበላሸት ፊልሙን በሙሉ ያቃጥላል።
አንዳንዴ ደግሞ ሰላይ እንዳይባል ካሜራውን ወደ ሰማይ ያደርግ ነበር። ሰዎች ሰማይ የሚያነሳ ነበር የሚመስላቸው። እሱ ግን አነሱን ነበር የሚያነሳው። እንደዛ ያነሳውን ፎቶ አሳይቶኛል።
ሙያው ባልታወቀበት ሰዓት አስተዋውቆ አስፋፍቶታል።
ይሄ አያቴን እንደ አዲስ እንዳየው ያደረገኝን የመጀመሪያ ፕሮጀክትን እኮራበታለሁ። እነዚህ ሥራዎች ጀርመን ሌሎች ፌስቲቫሎች ላይ አሳይቻለሁ።
‘ሴንተር ፎር ፎቶግራፊ’ የሚባል በማኅደር ኃይለሥላሴ የተጀመረ ፌስቲቫል ላይ ሄጄ አቅርቤዋለሁ።
2016 ላይ ‘አዲስ ፎቶ ፌስት’ ላይ ሄጄ ሳይ ሥራዬ እዚህ ይደርሳል ማለት ነው ብዬ አሰብኩ።
ከዚያ የሆነ ቀን ማለዳ ታዋቂዋ ፎቶግራፈር አይዳ ሙሉነህ ቢሮ ቀጥ ብዬ ሄድኩ።
ኮስተር ብዬ በቃ ካንቺ ጋር መሥራት እፈልጋለሁ፤ ‘አሳድጊኝ፤ ሜንተሬ እንድትሆኝ እፈልጋለሁ’ አልኳት።
በደንብ ሥራዎቼን አየችና ስለእኔ ጠየቀችኝ። ኤልፎራ እንደምሠራ ነገርኳት።
‘እዚያ የሚከፈልሽን እኔ እከፍልሻለሁ፤ ነይ’ አለችኝ። ያኔ ሚድሮክ፣ ኤልፎራ በመሥራቴ አባቴም ይኮራብኝ ነበር።
ቆራጥ ውሳኔ ወስኜ ሥራዬን እርግፍ አድርጌ ተውከት። ከአባቴ ጋር ትንሽ አልተስማማንበትም ነበር። እሱ ውሳኔዬን እንደ ውድቀት ነበር ያየው።
ግን በድፍረት አዲስ ዓለም ውስጥ ገባሁ።
አይዳ ሙሉነህ ጋር ስገባ ዐይኔ ተገለጠ። ፎቶ ማንሳት ብቻ ሳይሆን በፎቶ ታሪክ መንገር እንደሚቻል ተማርኩ። ‘ደስታ ፎር አፍሪካ’ የሚባለው ድርጅቷ ውስጥ ተቀጠርኩ።
ለአንድ ዓመት ያህል ፎቶ አላነሳሁም። ግን ፌስቲቫሉ ላይ በደንብ እሠራ ነበር።
ለምሳሌ የአንዲት የ16 ዓመት ኢትዮጵያዊት ቦክስ ተወዳዳሪን ፎቶ ዶክመንተሪ ፕሮጀክት ሠራሁ። ተወደደልኝ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኖቤል ሽልማት ሲያሸንፉ ኦስሎ ዐውደ ርዕይ ተዘጋጅቶ ነበር። እዛ ላይ ይሄኛውን ፕሮጀክት አሳየሁ።
የተለየ ታሪክ ያለው ስለሆነ ከአያቴ ቀጥሎ የምኮራበት ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱን ‘ካነን ስቱደንት ፕሮግራም’ አሸንፌበታለሁ።
የኒዮርክ ታይምስ፣ ዋሽንግተን ፖስት ላይ ያሉ ትልልቅ አርታኢዎች ፎቶውን አይተው አስተያየት ይሰጣሉ። የዋሽንግተን ፖስት አርታኢ ነበር ለኔ የደረሰኝ። ጥሩ ምላሽ ሰጥቶኛል። ይሄ ሥራዬ በኮትዲቫር ዋና ከተማ አቢጃንም ታይቷል።”

የፎቶው ባለመብት, Addis
ለፕሬዝዳንቷ ስለ አያቴ ነገርኳቸው’
‘ደስታ ፎር አፍሪካ’ ውስጥ እየሠራሁ ከፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ‘ፎቶግራፈር እንፈልጋለን’ ተብሎ እኔ ተጠራሁ።
ቃለ ምልልስ ተደርጎልኝ ተቀጠርኩ።
ይሄ አጋጣሚ ደግሞ ወደሌላ አቅጣጫ ወሰደኝ። ፎቶ ስጀምር አባቴ ብዙም ደስ አላለውም ነበር። ቤተ መንግሥት ስገባ ግን በጣም ኮራብኝ። ፎቶግራፊ የት እንደሚያደርሰኝ አየ። ቤተሰብም ደስ አለው።
ምክንያቱም ክብርት ሳሕለወርቅ ዘውዴ የመጀመሪያ ሴት ፕሬዝዳንት ናቸው። እንደ አርቲስት እሳቸው ጋር መግባቴ ልዩ ነበር።
ቢቢሲ፦ አያትሽ ግን ቤተ መንግሥት መግባትሽን ሲሰሙ ምን አሉ?
ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ስገባ ለአያቴ ተነግሮታል። በጣም ነው የተደሰተው። እኔ ሥራ በዝቶብኝ ስለነበር ኮንትራቴን ከመጨረሴ በፊት እሱጋ አልሄድኩም። በኋላ ግን አውርቼለታለሁ። እርጅና ስለሚጫነው ይረሳል። ሆኖም ተደስቷል።
ቢቢሲ፦ ከፕሬዝዳንቷ ሳሕለወርቅ ጋር ምን አወራችሁ?
መጀመሪያ ስንገናኝ ከአያቴ ጀምሮ ፎቶግራፈር እንደሆነን ነገርኳቸው።
እንዲያውም እኔ ሳልሆን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ ስለሺ ነው ‘አያቷም እናቷም ፎቶግራፈር ናቸው’ ብሎ የነገራቸው። ፕሬዝዳንቷ ‘እውነት?’ ብለው በጣም በመገረም ጠየቁ።
ከዛ ስለ አያቴም ስለ እናቴም ነገርኳቸው። ፊታቸው ላይ መደነቅን አይቻለሁ።
በአያቴ ዘመን የነበሩ ፊልሞችን እኔ ኤዲት አድርጌ በዲጂታል ስካን አድረጌ እንዳስቀመጥኩ ስነግራቸው፣ ‘እንደዛ ማድረግ እንደሚቻል አላወቅኩም ነበር። የኔንም የድሮ ፊልሞች እንደዛ ታደርጊልኛለሽ።’ አሉኝ።
ሥራ በዝቶባቸው ይሁን ወይ ፊልሙን ስላላገኙት መሰለኝ አልሰጡኝም። ግን ሐሳቡን ወደውት ነበር። ከንግግራቸው የተረዳሁት ታሪኮችን መሰነድ (archive) ላይ በጣም ጎበዝ ሴት እንደሆኑ ነው።
ታሪካዊ ፎቶዎች በዲጂታል ሳይሆን ታትመው ስም ተሰጥቷቸው መቀመጥ አለባቸው ብለው በጽኑ ያምናሉ።
አያቴ ውጫሌ ያነሳቸው ፊልሞች ዘመዶች ጥለውበታል። ‘አሁን ፊልም ጠፍቷል። ምን ያደርጋል’ ብለው አቃጥለውበታል። በጣም ነው ያዘንኩት። የተረፈውን ይዤ መጥቻለሁ። ታሪክ መሰነድ ወሳኝ ነገር ነው።

የፎቶው ባለመብት, Addis
‘ክብርት ሳሕለወርቅ ‘ትሁትና ቁጡ’ ናቸው’
‘’የመጀመርያዎቹ ቀናት ትንሽ አስጨናቂ ነበሩ። እንዴት ድንቅና ልዩ ፎቶ ላንሳ እያልኩ ስፈላሰፍ ነበር የማድረው።
በእርግጥ እሳቸው ጋር ተቀጥሬ ከመሥራቴም በፊት ብዙ ‘ኢቨንቶች’ ላይ አገኛቸው ነበር።
ያኔ ግን እሳቸውን ፎቶ ማንሳት ቀላል አልነበረም። ከሰኪዩሪቲዎች እየተሽሎኮለኩ ነበር የማነሳቸው። አሁን ነይና አንሺ ስባል ትንሽ ቀለል-ትንሽ ድንግር አለኝ።
ቢቢሲ፦በተለይ የመጀመርያው ፎቶ አላሳሰበሽም?
የመጀመርያ አሳይመንቴ የነበረው በጽሕፈት ቤታቸው እንግዳ ሲቀበሉ ማንሳት ነበር። የሚጠበቅብኝ በቃ የተለመደ ፎቶ አለ አይደል? ሲጨባበጡ፥ ቁጭ ብለው ሲወያዩ ምናምን? ማንሳት ነው። አንድ አምስት ፎቶዎች በቂ ናቸው።
እኔ ግን ‘ዩኒክ’ ፎቶ ለማንሳት ስለፈለ’ኩ በቃ አለ አይደል፣ በመስታወት አሻግሬ ምናምን ለማንሳት እታገል ነበር።
ከዚያ ቀደም ከነበሩ ፎቶ ባለሙያዎች የተሻልኩና ልዩ እንደሆንኩ ማሳየት ነበር ሐሳቤ። ገባህ? አልተሳካልኝም።
ብቻ ያን ቀን አንስቼ ወጣሁ። መጀመርያ ስብሰባውን ሙሉ አብርያቸው የምሆን ነበር የመሰለኝ። ለካንስ 5 ደቂቃ ገብተህ አንስተህ ውልቅ ማለት ነው ያለብህ።
ዝም ብዬ ነበር የደከምኩት። የኔ ‘ኤክስትራ ኤፈርት’ ትርጉም አልነበረውም።
ቢቢሲ፦ ፎቶዎችን የምትመርጪው አንቺ ነሽ?
አይደለሁም። በኮሚኒኬሽን ቲም ነው የሚመረጡት። የቱ ፎቶ ለሕዝብ እንደሚታይ እኔ አልወስንም፤ የኔ ሥራ ማንሳት ብቻ ነው።
ቢቢሲ፦ አንቺም ፕሬዝዳንቷም ፎቶዎቹን አትመርጡም ማለት ነው?
የኔ ሥራ እንዳልኩህ ማንሳት ብቻ ነው። የኮሚኒኬሽን ቢሯቸው መርጦ ያሳለፈውን ግን ፕሬዝዳንቷ ያጸድቁታል።
ቢቢሲ፦ ስለዚህ አንቺ ድንቅ ፎቶ አንስቻለሁና ይሄ ይሁን ማለት እትችይም?
እንደዚያ ብሎ ነገር የለም። የዲፕሎማቲክ ፕሮቶኮል የጠበቁ የፎቶ ዓይነቶች አሉ። በቃ እነሱ ናቸው የሚፈለጉት። የኔ በተለየ መንገድ ልዩ ፎቶ ማንሳት ትርጉም የለውም የምልህ ለዚያ ነው።
እንዲያውም ከቤተ መንግሥት ውጭ ለበዓላት እንደዚህ አደባባይ ሲወጡ የተሻሉ ፎቶዎችን የማንሳት ነጻነት ነበረኝ።
የቢሮ ፎቶዎች ፍጥነት ብቻ ነው የሚፈልጉት። ሲጨባበጡ እንዳያመልጥህ፤ ከዚያ ውጭ ምንም የተለየ ነገር አይፈልግም።
ለምሳሌ የኡጋንዳ በዓለ ሲመትን ሲታደሙ ወደዚያ ሄደን ነበር። የተሻለ ፎቶ ማንሳት የቻልኩት እዚያ ነው።
ቤተ መንግሥት ‘ክርኤቲቭ’ መሆን አትችልም። በቃ ምን ልበልህ፤ ካሜራ የያዘ ወታደር ነህ። በጣም ፎርማል ፎቶዎች ናቸው የሚፈለጉት።
በዚያ ላይ እንደፈለክ መሆን አትችልም፤ ፕሮከቶኮል ይገድብሃል። አሁን ከቤተ መንግሥት ወጥቼ ያለኝን ነጻነት እወደዋለሁ።

የፎቶው ባለመብት, Addis
ቢቢሲ፦ የርሳቸው የግል ፎቶግራፈር ሆነሽም እሳቸውን ማግኘት ቀላል አልነበረማ።
አዎ። ቀላል አይደለም። እሳቸው ግን በተቻለ ሰውን ያቀርባሉ። የግል ፕሮግራምም ሲኖራቸው ‘ዐዲስን ጥሯት እስኪ ትምጣ’ ብለው ያስጠሩኝ ነበር።
ቢቢሲ፦ እሳቸው አጠር ያሉ ናቸው። ጥበቃዎቻቸው ደግሞ ዘለግ ያሉ ናቸው። ፎቶ ለማንሳት አትቸገሪም?
ደስ በሚል ሁኔታ ከእርሳቸው ጋር ቁመታችን እኩል ነው። (ሳቅ) እንዲያውም ጋርዶች ይስቁብኝ ነበር። ምክንያቱም ሳነሳ አልታያቸውም። ፕሬዝዳንቷን እያነሳኋቸው ራሱ ‘የታለች ዐዲስ?’ ብለው ይፈልጉኛል። (ሳቅ)
አንዴ ምን ሆነ መሰለህ? ቢሮ የሆነ ጊዜ ተንበርክኬ ፎቶ እያነሳሁ ጋርዳቸው ከልሏቸው ነው መሰለኝ ‘ዐዲስ የታለች? ዛሬ ፎቶ አታነሳም እንዴ?’ አሉ።
ጋርዶቹ ሲፈልጉኝ ለካንስ እኔ ከሥር ሆኜ እያነሳሁ ነበር። ነገሩ አሳቃቸው። እኔም እንደርሳቸው አጭር መሆኔ ሳይጠቅመኝ አልቀረም (ሳቅ)
ቢቢሲ፦ ሴት ሆኖ ፎቶግራፈር መሆን ከባድ ነው?
ይሄ በሁሉም ዘርፍ ላለች ሴት የሚጠየቅ ጥያቄ ነው። ለኔ ግን በተቃራኒው ነው። ሴት በመሆኔ ሰዎች ሰላማዊ ናት ብለው ያስቡኛል። የጸጥታ ሰዎች ሴት በመሆኔ ያሳልፉኛል።
የአደባባይ ፎቶ ሳነሳ ለምሳሌ ሰዎች ‘አግሬሲቭ’ አይሆኑብኝም፤ ሴት ስለሆንኩ።
አዲስ አበባ አንድ ወንድ ፎቶግራፈር ፎቶ ሲያነሳ ብዙ ሰው ለጸብ ይጋበዛል፤ እኔን ግን ያልፉኛል። ሴት በመሆኔ።
ወታደሮች ለምሳሌ መሪዎችን ሲጠብቁ ይገፈታትሩሃል ምናምን። እኔ ግን እታለፋለሁ። አድቫንቴጅ ነው ሴት መሆኔ።
ቢቢሲ፦ ክብርት ፕሬዘዳንት ፎቶ ይወጣላቸዋል? ‘Photogenic’ ናቸው?
እኔ ብዙውን ጊዜ በመደበኛ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው ስለማነሳቸው ይህን ለማለት ይከብደኛል። አንድ ነገር የምነግርህ ግን እሳቸው ለፎቶ አውንታዊ አመለካከት ነው ያላቸው። ፎቶ ለመነሳት ችግር የለባቸውም። ፎቶ ይወዳሉ። ጠቃሚ ነገር ነው ብለው ያስባሉ። ያ ደስ ይለኛል።
ቢቢሲ፡ ምን ማለት ነው ይሄ?
በቃ ፎቶ መሰነድ አለበት ብለው ያምናሉ። በፎቶ መቅረት ያለባቸው ነገሮች ፎቶ መነሳት እንዳለባቸው ያምናሉ። ምናልባት በተባበሩት መንግሥታት ሥራ ውስጥ ስላለፉ የፎቶን ጥቅም ይረዳሉ ብዬ አስባለሁ። የፎቶ ኮሚኒኬሽን ዋጋ እንዳለው ይረዳሉ። ለፎቶ መረጃ፣ ለፎቶ ኮሚኒኬሽን በጎ አመላከት እንዳላቸው ስለማውቅ ያ ደስ ይለኛል።
ቢቢሲ፦ እንደ ግል ፎቶግራፈራቸው ፕሬዝዳንቷን በቅርብ ታውቂያቸዋለሽ ተብሎ ይገመታል። እኛ በቴሌቪዥን ነው የምናውቃቸው። ምን ዓይነት ሴት ናቸው?
በጣም ፕፎፌሽናል ሴት ናቸው። ወታደራዊ ዲሲፕሊን ነው ያላቸው። ለጥቃቅን ነገሮች ዓይን አላቸው። ሴት ስለሆኑ ማኅበረሰቡ እንዲሆኑ የሚጠብቀው ነገር አለ አይደለ? መለሳለስ እንደዚህ። እሳቸው ግን በጭራሽ። ከወንዶችም በላይ ቁጡ ናቸው። ሥራቸው ላይ ወለም ዘለም አያውቁም። ቆፍጣና ናቸው።
ቢቢሲ፦ በቴሌቪዥን ስናያቸው ግን ለስላሳና ገራገር ሴት ነው የሚመስሉት እኮ።
ልክ ነህ። ሁለቱንም መልካቸውን አይቻለሁ። ሥራ ሲሆን በቃ ምንም ቀልድ አያውቁም። ቁጡ ሆነው፤ ኮስተር ብለው ሥራውን ያሠራሉ። መጀመርያ ሥራው እንዲሠራ ነው የሚሹት። ሥራ ከተሠራ በኋላ ደግሞ በጣም ተጫዋችና ለስላሳና ደርባባ (Charming) ሴት ይሆናሉ። ግርማ ሞገስ አላቸው። ሲያወሩህ ትሁት (humble) ሆነው ነው የሚያዋሩት። passionate ናቸው።
ቢቢሲ፦ ይሄ ፎቶ ይሰረዝልኝ ብለውሽ ያውቃሉ?
አላስታውስም።
ቢቢሲ፦ ወዳንቺ እንምጣ፤ የፎቶግራፍ ጥበብ ሕይወትሽን ፍሬም ሰጥቶታል?
ፎቶግራፊ ዓለምን የማይበት መንገድ ቀይሮታል። ካሜራ ይዤ መንገድ ላይ ስሄድ ‘ዲቴይል’ ነው የማየው። ካሜራ አንስተህ አይደለም የምታየው። አይተህ ነው ካሜራ የምታነሳው።
ለምሳሌ ሰው ታሪክ ሲያወራልኝ አእምሮዬ ‘አውቶማቲካሊ’ የሚያስበው ይሄ ታሪክ በፎቶ እንዴት ይገለጻል ብሎ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Addis
ቢቢሲ፡ ድንቅ ፎቶ የሚባለው እንዴት ያለ ፎቶ ነው?
አሪፍ ፎቶ ‘wow moment’ ያለው ፎቶ ነው። ‘አሃ’ የሚያስብል ነው። አሪፍ ፎቶ ታሪክ መናገር የሚችል ፎቶ ነው።
ቢቢሲ፦ ላንቺ ከኢትዮጵያ መሪዎች ምርጡ ፎቶ የትኛው ነው?
ሽመልስ ደስታ ያነሳቸው ፎቶዎች ለኔ ድንቅ ናቸው። በጣም የምወደው ደግሞ ጃንሆይ ቤታቸው ዉሻ ሲያጫውቱ ያነሳቸውን ነው።
ቢቢሲ፦ ለምንድነው የምትወጂው ያን ፎቶ?
በቃ ያን ፎቶ ሳየው የንጉሡን ሰዋዊ ገጽታ ያሳየኛል። ‘Candid moment’ ነው። ደስ ይለኛል።
ቢቢሲ፦ ካነሳሻቸው ፎቶዎች ሁሉ የላቀ የምትይው የቱን ነው?
ለመጀመርያ ጊዜ አያቴን ያነሳሁት ‘ፖርትሬይት’ ፎቶ አለ። እሱን በጣም እወደዋለሁ።
ቢቢሲ፦ ወደፊት ቴክኖሎጂ ሲራቀቅ ፎቶ ጥበብን የሚያከስመው ይመስልሻል?
ያሳስበኛል። ሁሉ ነገር ሰው መሆኑ ቀርቶ ማሽን እየሆነ ነው። ሰዎች ሲያገኙኝ ቀድመው የሚጠይቁኝ የካሜራዬ ዓይነት ነው። በያሺካ የተነሱት የአያቴ ሥራዎች ግን ይበልጥ ጉልበት አላቸው። ከኔ የዲጂታል ዘመን ፎቶ ይልቅ ማለቴ ነው። በዚህ ዘመን ሚሊዮን ፎቶ ልታነሳ ትችላለህ። ፕሪነት አድርገህ የምታወጣው ፎቶ ግን ብዙ አይደለም። ታየዋለህ ቅርስ (Treasure)ነው።
ቢቢሲ፦ ‘ትክክለኛው የኛ ፎቶ የምንደምስሰው ፎቶ ነው’ የሚባለውን ነገር እንዴት ታይዋለሽ?
ለኔ ትክክለኛ ፎቶ አንድ ሰው መነሳቱን ሳያውቅ የሚነሳ ፎቶ ነው። ካሜራ ረስተህ የምትነሳው ፎቶ ሕይወት አለው። ‘Invisibility moment’ እንላታለን። እውነተኛ ማንነት በዚያ ቅጽበት ያለችው ናት።
ቢቢሲ፦ ወደፊት ፎቶግራፈሩ ሆኜ ብሠራ የምትይው ታላቅ መሪ አለ/አለች? ወይም ዝነኛ ሰው?
እሱን ምዕራፍ ያለፍኩትት ይመስለኛል። ዐይን ያልበዛበትን ሴት አግኝቼ በፎቶ ታሪኳን መናገር ብችል ነው ከዚህ ወዲያ ደስ የሚለኝ።
ቢቢሲ፦ የክብርት ሳሕለወርቅ የግል ፎቶግራፈር ሳለሽ ምን ያህል ገንዘብ ይከፈልሽ ነበር?
ብዙም አይደለም፤ ትንሽም አይደለም። በዚያ እንለፈው።
ቢቢሲ፦ እኮ ያ ማለት ምን ያህል ነው?
ይልቅ አሁን ከዚያ ከወጣሁ በኋላ ዕለታዊ ዋጋ ተመኔን ልነግርህ እችላለሁ። 500 ዶላር ነው ለአንድ ቀን ሥራ የማስከፍለው።
ቢቢሲ፦ የአዲስ ዓመት ቀጣዩ ህልምሽ ወዴት የሚወስድ ነው?
የቤተሰቡን የፎቶግራፍ ሌጋሲ ለማስቀጠል ከታናሽ እህቴ ጋር ‘አእምሮስ’ (Aemero) የሚል ስቱዲዮ ለመክፈት ሐሳብ አለን። ገና ሐሳብ ነው።
ቢቢሲ፦ አዲስ፤ መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልሽ
አመሰግናለሁ።

የፎቶው ባለመብት, Addis












