የሰሜን ኮሪያው ኪም ጥይት የማይበሳቸው 20 ተሽከርካሪዎችን ጭነው ሩሲያ ገቡ

ኪም ጆንግ ኡን

የፎቶው ባለመብት, REUTERS

የምስሉ መግለጫ, ኪም ጆንግ ኡን

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የሩሲያን ድንበር አልፈው ገቡ።

ኪም ወደ ሩሲያ ያቀኑት ፑቲንን ለማግኘት ነው።

ሁለቱ መሪዎች በተለይ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ለከፈተችው ጦርነት የጦር መሣሪያ ከሰሜን ኮሪያ የምታገኝበትን መንገድ ይመክራሉ ተብሏል።

የሰሜን ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ ማክሰኞ እንዳረጋገጠው ኪም የተሳፈሩበት የጦር ባቡር የሩሲያን ድንበር አልፎ ገብቷል።

ኪም አሁን የሩሲያን ድንበር አልፈው ወደ ወደብ ከተማዋ ቪላዲስቮስቶክ በማቅናት ላይ ናቸው።

ይህ ዘገባ ሲጠናቀር ኪም በጉዞ ላይ ሲሆኑ እዚያ የሩሲያ ከተማ ለመድረስ 6 ሰዓታት ያህል ሊወስድባቸው ይችላል።

ኪም ከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸውን አስከትለው ነው ወደ ቪላዲስቮስቶክ እያቀኑ ያሉት።

ከሰሜን ኮሪያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የወጡ ምሥሎች ኪም ከፒዮንግያንግ በጦር ባቡር ሆነው እጃቸውን እያውለበለቡ ሸኚዎቻቸውን ሲሰናበቱ የሚያሳዩ ናቸው።

ፒዮንግያንግ ለሞስኮ የጦር መሣሪያ ታቀርባለች ወይ? በምን ያህል መጠን? ምን ዓይነት መሣሪያዎች? በምላሹስ ከሩሲያ ምን ታገኛለች የሚለው ምዕራባዊያንን ያስጨነቀ ጉዳይ ነው።

ኪም ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ቪላዲቮስኮኦቭ ያመሩት እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2019 ወር ፑቲንን ለማግኘት ነበር።

ኪም ከያኔው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ተገናኝተው ውይይታቸው ፍሬ ሳያፈራ በመቅረቱ ነበር ቀጥለው ወደ ፑቲን አገር ሩሲያ የተጓዙት።

ኪም አሁን እየተጓዙበት ባለው የጦር ባቡር ወደ 20 የሚሆኑ ጥይት የማይበሳቸው መኪናዎች ጭነዋል ይላሉ ምንጮች።

ይህም የሚጓዙበት ባቡር ክብደቱ በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ስላደረገው በፍጥነት ለመጓዝ ተስኖት በዝግታ ነው ወደ ቪላዲቮስኮቭ እያመራ ያለው።

ባለሙያዎች እንደሚሉት የኪም ባቡር አሁን በሰዓት እየተጓዘ ያለው 59 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው።

ዋይት ሐውስ ኪምና ፑቲን በጦር መሣሪያ ዙርያ ስምምነት እንደሚደርሱ መረጃ አለኝ ብላለች።

ሩሲያ ከኮሪያ ሮኬቶችና ሌሎች መለስተኛ የጦር መሣሪያዎች ካገኘች በገንዘብ፣ በማዕድን ጥሬ ዕቃና በምግብ ሰሜን ኮሪያን ልትክስት ትችላለች ይላሉ ዲፕሎማቶች።

ሩሲያ 122ሚሚ እና 152 ሚሚ ተተኳሽ ሚሳኤሎች ከመጋዘኗ እየተመናመኑ ስለሆነ ይህን ከሰሜን ኮሪያ ማግኘት ትፈልጋለች።

በሐምሌ ወር የሩሲያው መከላከያ ሚኒስትር ሾይጎ ከኪም ጋር ፒዯንግያንግ በተገናኙ ጊዜ የጦር መሣሪያ ክምችታቸውን አስጎብኘተው ነበር።

ኪም ለአንድ የውጭ አገር ባለሥልጣን የጦር መሣሪያ ሲያስጎበኙ የሩሲያው መከላከያ ሚኒስትር የመጀመርያው ናቸው።