ሊቢያ፡ በሺህ የሚቆጠር አስክሬን 100 ኪሎ ሜትር ድረስ በጎርፍ ተወስዷል

እንደ ተመድ ከሆነ እስከ 1ሺህ ሰዎች በጅምላ መቃብር ተቀብረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, እንደ ተመድ ከሆነ እስከ 1ሺህ ሰዎች በጅምላ መቃብር ተቀብረዋል።

በሊቢያ በደረሰው የጎርፍ አደጋ የሟቾች ቁጥር በየዕለቱ እያሻቀበ ነው።

ከአምስት ቀናት በፊት በደረሰው በዚህ የጎርፍ አደጋ ከ11ሺህ በላይ ሰዎች እንደሞቱ ይገመታል። ምናልባት ቁጥሩ ከዚህ እጥፍ ሊደርስ ይችላል።

ምን ያህል ሕዝብ ነው የሞተው በሚለው የተለያዩ ምንጮች የተለያዩ አሐዝ ያስቀምጣሉ።

መንግሥት እስከትናንት ድረስ የሟቾች ቁጥር ሦስት ሺህ እንደሆነ ነው የማውቀው ብሏል።

በተባበሩት መንግሥታት የሊቢያ አምባሳደር ይህን ቁጥር እጥፍ ከፍ ያደርጉታል።

የዓለም የቀይ ጨረቃ ማኅበር ደግሞ 11ሺህ ሰዎች ነው የሞቱት ይላል።

በጎርፍ አደጋው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት የደርና ከተማ ከንቲባ በበኩላቸው 20ሺህ ሰዎች ነው የሞቱት ይላሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት ሊቢያዊያን አስክሬን በጀምላ መቅበር እንዲያቆሙ ተማጽኗል።

ከአንድ ሺህ በላይ አስክሬኖች በጅምላ ተቀብረዋል ይላል የተባበሩት መንግሥታት ዘገባ።

የዓለም ጤና ድርጅት አስክሬኖች ለቀብር በተከለለና በውል መለየት በሚቻል ውስን ቦታ ሟቾች ካልተቀበሩ የጀምላ ቀብር ኋላ በቤተሰቦች ላይ ዘላቂ ጠባሳ ጥሎ ያልፋል ሲል ስጋቱን ገልጧል።

በደርና ከተማ በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ደብዛቸው አሁንም እንደጠፋ ነው።

በሺህ የሚቆጠሩ አስክሬኖች ደግሞ በጎርፍ እስከ መቶ ኪሎ ሜትር ድረስ ተወስደው ባሕር ዳርቻ ላይ ተንሳፈው ይገኛሉ ይላሉ ዘገባዎች።

ቡልዶዘሮች የደርና መንገዶችን ፍርስራሽ እያነሱ ቢሆንም ሥራው አዝጋሚና ተስፋ አስቆራጭ ነው። አሁንም ድረስ ከፍርስራሾች ሥር አስክሬኖች ይኖራሉ።

በአንዳንድ ቦታ የአስክሬን እጅና እግር ምልክት ሲገኝ ሰዎች አስክሬኑ የቤተሰባቸው አባል ይሆናል በሚል ጎትተው ካወጡ በኋላ ማንነቱን ለመለየት የሚሞክሩበት መንገድ እጅግ አሳዛኝና የከፋ ስሜትን የሚፈጥር ሆኗል።

የተባበሩት መንግሥታ አንድ ከፍተኛ የረድኤት ጉዳዮች ኃላፊ የአየር ንብረት ለውጥና የሊቢያ መንግሥት ችግሮችን ለመቋቋም ያለው ዝግጁነት አናሳ መሆን ሁኔታዎች የከፉ እንዲሆኑ አድርጓል ይላሉ።

በርካታ አስክሬኖች100 ኪሎ ሜትር ድረስ በጎርፉ ተወስደው ባሕር ዳርቻ ብቅ እያሉ ነው
የምስሉ መግለጫ, በርካታ አስክሬኖች100 ኪሎ ሜትር ድረስ በጎርፉ ተወስደው ባሕር ዳርቻ ብቅ እያሉ ነው

በሊቢያ የቀይ መስቀል ኃላፊ ታሚር ረመዳን የረድኤት ሠራተኞች በጭቃ ውስጥ ገብተው፣ ፍርስራሽ በእጃቸው ጭምር እያፈሱ ነፍስ ለመታደግ ቀን ተሌት እየሠሩ ነው ብለዋል።

“አሁንም ተስፋ አለ፣ ተስፋ ሁሌም አለ፣ በሕይወት የሚኖር ሰው ይኖራል ብለን ተስፋ ማድረጋችንን አንተውም’’ ይላሉ ረመዳን አደጋው ከደረሰ አምስት ቀናት ቢያልፉም።

የዓለም ቀይ ጨረቃ ማኅበር 11ሺህ ሊቢያዊያን መሞታቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል። 20ሺህ ደግሞ ደብዛቸው እንደጠፋ መረጃ አለኝ ይላል።

አስክሬኖች በጎርፍ 100 ኪሎ ሜትር ድረስ መወሰዳቸውና ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ መውጣታቸው ምናልባት ከዚህ ወዲያ ደግሞ ወረርሽኝ ይከሰት ይሆን የሚል ፍርሃት ፈጥሯል።

ነገር ግን የዓለም ቀይ መስቀል ማኅበር የአስክሬን ምርመራ ባለሙያ አስክሬኖች በብዛት በመንገድ ላይ መገኛታቸው በራሱ የሚፈጥረው የወረርሽኝ አደጋ አናሳ ነው ይላሉ።

ከዚያ ይልቅ ከተፈጥሮ አደጋ ማግስት በማኅበረሰብ ውስጥ ከንጽህና ማነስ የሚፈጠር አስከፊ ሁኔታ ወረርሽኝ ሊጭር ይችላል ብለው ይሰጋሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ የዉሃ ምንጭ አመጠገብ የተጣሉ አስክሬኖች የጤና እክል ሊፈጥሩ ይችላሉ ሲል ስጋቱን አስቀምጧል።

በሊቢያ፣ ደርና በምትባል ጠረፋማ ከተማ ግድብ ጥሶ የወጣ ጎርፍ ባስከተለው በዚህ አደጋ ከ30ሺህ ሰዎች በላይ ተፈናቅለዋል።

የዓለም አየር ትንበያ ማኅበር በሊቢያ በአግባቡ የሚሠራ የአየር ትምበያ አገልግሎት ቢኖር ይህ አደጋ ሳይደርስ መታደግ ይቻል ነበር ብሏል።