የፍልስጤም 'ማንዴላ' የሚባለው ማርዋን ባርጉቲ ማን ነው? ከሰሞኑ ስምምነት ጋር ስሙ ለምን ተነሳ?

ማርዋን ባርጉቲ በእስር ቤት ጠባቂዎች ታጅቦ የድል ምልክት ሲያሳይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ማርዋን ባርጉቲ በእስር ቤት ጠባቂዎች ታጅቦ የድል ምልክት ሲያሳይ

ፍልስጤማዊው ፖለቲከኛ ማርዋን ባርጉቲ የፋታህ ንቅናቄ መሪ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በእስራኤል እስር ቤት ይገኛል። ባርጉቲ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ከተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ጋር ተያይዞ ወሳኝ ሰው እየተባለ ነው።

በስምምነቱ መሠረት ከሐማስ እገታ በሚለቀቁ እስራኤላውያን ምትክ ከሚፈቱ በርካታ ፍልስጤማውያንን መካከል አንዱ መሆኑም እየተነገረ ነው። ለመሆኑ ባርጉቲ ማን ነው? የእሱ መፈታትስ ለምን ጠቃሚ እና አከራካሪ ሊሆን ቻለ?

ማርዋን ባርጉቲ በ15 ዓመቱ የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ የጀመረው በፍልስጤም ነጻነት ድርጅት ፋታህ እንቅስቃሴ ውስጥ ነው። ንቅናቄው ይመራ የነበረው በሟቹ የፍልስጤም መሪ ያሲር አራፋት የነበረ ሲሆን፣ የተመሠረተውም ለፍልስጤም አገር የመሆን እንቅስቃሴ ድጋፍ በማሰባሰብ ነበር።

ባርጉቲ የሁለተኛው የፍልስጤማውያን ሕዝባዊ አመጽ ኢንቲፋዳ መሪ በመሆን ታዋቂነትን ያተረፈ ሲሆን፣ በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አሳልፏል።

ባርጉቲ በአውሮፓውያኑ በ2002 እስራኤል 'የመከላከያ ጋሻ' በማለት በሰየመችው ዘመቻ በቁጥጥር ስር ዋለ። ባርጉቲን የአል-አቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ የሚባለውን የፍልስጤማውያን ወታደራዊ እንቅስቃሴን አቋቁሟል በማለት እስራኤል ብትይዘውም እሱ ግን ክሱን ውድቅ አድርጓል።

የአል-አቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ የእስራኤል ወታደሮችን፣ ሰፋሪዎችን እና ሠላማዊ ዜጎችን የገደሉ ተከታታይ ጥቃቶችን ፈጽሟል።

በጥቃቶቹ ምክንያት ከተላለፈበት የ40 ዓመት እስር በተጨማሪ እአአ በ2004 አምስት የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።

የፍልስጤማዊው መሪ በፍርድ ሂደቱ ወቅት የእስራኤልን ፍርድ ቤት ሥልጣንን ለመቀበል ፈቃደኛ ካለመሆኑም በላይ የቀረቡበትን ክሶች ሁሉ ውድቅ አድርጓል።

ፍልስጤማዊቷ ጠበቃ እና ባለቤቱ የሆነችው ፋድዋ ባለፈው ዓመት ለቢቢሲ እንደገለጸችው "የተከሰሰው እነዚህን ድርጊቶች በቀጥታ በመፈጸሙ ሳይሆን፣ መሪ በመሆኑ ነው" በማለት ገልጻለች። ባርጉቲ በምርመራው ወቅት የአል-አቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ "መመሥረት" የሚለውን ክስ ውድቅ ማድረጉንም ገልጻለች።

ይህ በባርጉቲ ላይ የቀረበው ክስ ስሙ በፍልስጤማውያን ዘንድ እንዲናኝ አድርጎታል። በርካታ ፍልስጤማውያንም እንደ ኔልሰን ማንዴላ ይቆጥሩታል። ማህሙድ አባስን በመተካት የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሆኖ ይሾማል ተብሎም በሰፊው ይታሰባል።

ይህ ግን የሚሳካው ከእስራኤል እስር ቤት በመፈታቱ ላይ ነው።

ከአገር የመባረር ዕጣ ፈንታ

ሟቹ የፍልስጤም መሪ ባርጉቲ ከእስር እንዲለቀቅ የሚጠይቅ ፖስተር ይዘው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሟቹ የፍልስጤም መሪ ባርጉቲ ከእስር እንዲለቀቅ የሚጠይቅ ፖስተር ይዘው
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አንዳንድ የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ብዙ ፍልስጤማውያን ማህሙድ አባስን በመተካት የፍልስጤም ፕሬዚደንት ሊሆን እንደሚችል የሚያስቡትን ግለሰብ እስራኤል ልትለቅ ትችላለች። ይህ የሚሆነው ግን ባርጉቲ "ከፍልስጤም ግዛቶች ውጪ ይባረራል" በሚል ቅድመ ሁኔታ ነው።

የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያ የሆኑት አኒስ አል ቃሴም ለቢቢሲ አረብኛ እንደተናገሩት ከሆነ ባርጉቲ ከፍልስጤም ግዛቶች እንዲወጣ መደረጉ ከውጭ ሆኖ የፍልስጤም መንግሥት ፕሬዝዳንት ከመሆን የሚያግደው ነገር የለም ብለዋል።

ቀደም ሲል በታሪክ በተለይም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በስደት ላይ ያሉ መንግሥታት ነበሩ። የፍልስጤም ሕገ መንግሥት እና ሕጎችም ይህንን አይከለክሉም።

እስራኤል ባርጉቲን እንዲሰደድ የምታደርግበት ምክንያት "ፍልስጤማዊው መሪ በተለይም በፋታህ እንቅስቃሴ ውስጥ ሰፊው ተቀባይነት ያለው በመሆኑ ነው" ብለዋል አል ቃሴም።

በአውሮፓ ኅብረት በከፊል የሚደገፈው የፍልስጤም የፖሊሲ እና የዳሰሳ ጥናት ማዕከል እአአ በ2023 ባሰባሰበው የሕዝብ አስተያየት ማርዋን ባርጉቲ ለፍልስጤም ፕሬዝዳንትነት ቀዳሚ ተመራጭ እንደሚሆን አሳይቷል።

የሕዝብ አስተያየቱ እንደሚያሳየው ከሆነ በወቅቱ ባርጉቲ፣ የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ እና የሐማሱ መሪ ኢስማኢል ሃኒያ (ባለፈው ዓመት ሐምሌ ቴህራን ውስጥ ተገድለዋል) ዕጩዎች ሆነው አዲስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቢካሄድ ባርጉቲ 47 በመቶ፣ ሃኒያ 43 በመቶ እና አባስ 7 በመቶ ድምጽ ያገኙ ነበር።

ባርጉቲ በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2021 በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይወዳደራል ተብሎ ሲጠበቅ ነበር። እስራኤል ምርጫው በምሥራቃዊ ኢየሩሳሌም እንዲካሄድ አልፈቀደችም በሚል ምክንያት አባስ ምርጫውን ሰርዘዋል።

'የሚያግባባ ዕጩ'

ባርጉቲ ከእስራኤል ጋር ሰላም እንዲሰፍን እና ከ1967 በፊት ባሉት ድንበሮች ላይ የተመሠረተ የሁለት አገር መፍትሔን እንደሚደግፍ ተናግሯል።

በአውሮፓውያኑ 2002 ለዋሺንግተን ፖስት እንደጻፈው ከሆነ "እኔ እና አባል የሆንኩበት የፋታህ እንቅስቃሴ በወደፊት ጎረቤታችን እስራኤል ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን እና ሰላማዊ ሰዎች ዒላማ መደረጋቸውን አጥብቀን የምንቃወም ቢሆንም፤ እራሴን የመከላከል መብቴን፣ የእስራኤል ወረራ መቃወሜን እና ለነጻነቴ የመታገል መብቴን አሳልፌ አልሰጥም" ብሏል።

ጨምሮም "አሁንም እስራኤል በ1967 (እአአ) ከያዘቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች ወጥታ በሁለቱ እኩል እና ነጻ በሆኑት የእስራኤል እና የፍልስጤም መንግሥታት መካከል በሰላም አብተው እንዲኖሩ እሻለሁ" ብሏል።

"በግልጽ ለመናገር እኛ የምንፈልገው ዓለም አቀፉ ሕግ ተግባራዊ እንዲሆን ብቻ ቢሆንም፣ ለእስራኤል ግትርነት ሁልጊዜም ተወቃሽ መሆን ሰልችቶናል።"

ከአውሮፓውያኑ 2002 ጀምሮ በእስራኤል ታስሮ የሚገኘው ባርጉቲ የፍልስጤምን አስተዳደር በመረከብ አገር ለመሆን እንድትዘጋጅ ሁሉንም "የሚያስማማ ምርጫ" ሊሆን ይችላል።

ምንም እንኳን በአምስት ሰዎች ግድያ የተከሰሰ እና "በእጁ ላይ ደም አለበት" የሚሉ እስራኤላውያን የባርጉቲን የመልቀቅ ሀሳብ ባይቀበሉትም፤ ሌሎች ደግሞ የእሱ መፈታት በፍልስጤማውያን መካከል የጋራ መግባባት ለመፍጠር፤ ተቀናቃኝ ቡድኖችን አንድ በማድረግ ለሰላም የተሻለ ተስፋ እንደሚሰጥ ያምናሉ።

እስራኤላዊው ፀሐፊ ጌርሾን ባስኪን በ2024 ሃሬትዝ በተባለው እስራኤል ጋዜጣ ላይ እንደፃፉት ከጋዛ ጦርነት በኋላ በሚኖረው የሽግግር ጊዜ "የፍልስጤም አንድነትን ለማጠናከር እና ክልሉን ከወታደራዊ ቀጣናነት ነጻ ለማድረግ ቁርጠኛ የሆነ የፍልስጤም መሪ ያስፈልገዋል። ይህ መሪ ደግሞ ባርጉቲ ሊሆን ይችላል።"

እስራኤልን ከዌስት ባንክ በሚለየው ግንብ ላይ የተሳለ የባርጉቲ ምሥል

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እስራኤልን ከዌስት ባንክ በሚለየው ግንብ ላይ የተሳለ የባርጉቲ ምሥል

ማርዋን ባርጉቲ በአውሮፓውያኑ 1958 በራማላህ ከተማ አቅራቢያ በምትገኝ ኮባር መንደር ነበር የተወለደው።

በ1967 በተካሄደው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ወቅት እስራኤል ዌስት ባንክን እና ምሥራቅ እየሩሳሌምን ስትቆጣጠር ዘጠኝ ዓመቱ ነበር።

ባርጉቱ ከ15 ዓመቱ ጀምሮ በሟቹ ያሲር አራፋት በሚመራው ፋታህ እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ አድርጓል።

በ1978 ደግሞ የታጣቂ የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን አባል ሆኗል በሚል በእስራኤል ተይዞ ከአራት ዓመታት በላይ ታስሮ ነበር።

ባርጉቲ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እና የዕብራይስጥ ቋንቋን የተከታተለው በእስር ቤት ሳለ ነበር። በ1983 ከእስር ከተለቀቀ በኋላ በቢርዘይት ዩኒቨርሲቲ ለዲግሪ መማር ጀመረ።

ሆኖም ትምህርቱን ለመጨረስ ተጨማሪ 11 ዓመታት ፈጅቶበታል። በፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በመቆየቱ እና የፋታህ "ወጣት ዘብ" ግንባር ቀደም አባል በመሆን ንቅናቄው ያቋቋሙትን አራፋት እና አባስን ጨምሮ አመራሮቹ በሊባኖስ እና ቱኒዝያ በግዞት ሲሰዱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ በቃ።

ከዚያም እአአ በ1987 ፍልስጤማውያን የእስራኤልን ወረራ በመቃወም የመጀመሪያውን ኢንቲፋዳ ወይም አመጽ ቀሰቀሱ። ባርጉቲ በዌስት ባንክ መሪ ሆኖ ብቅ አለ። በኋላም ወደ ዮርዳኖስ ተባረረ። የ1994 የኦስሎ የሰላም ስምምነትን ተከትሎ ተመለሰ። የሰላም ሂደቱን አጥብቆ ቢደግፍም ግን እስራኤል በተከታታይ ለሚደረጉት የመሬት የሰላም ስምምነቶች ላይ ያላትን ቁርጠኝነት ሲጠራጠረው ቆይቷል።

በመስከረም 2000 (እአአ) ሁለተኛው ኢንቲፋዳ ሲፈነዳ ባርጉቲ የዌስት ባንክ የፋታህ መሪ እና የቡድኑ ታጠቂ ክንፍ የሆነው የታንዚም ዋና መሪ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2001 የባርጉቲ የግል ጠባቂ መኪና በሚሳዔል በተመታበት ጊዜ በእስራኤል ከተሞከረበት ግድያ አምልጧል።

ባርጉቲ ጠበቃዋን እና የፖለቲካ አክቲቪስቷን ፋድዋን አግብቶ አንድ ሴት እና ሦስት ወንዶች ልጆች አሉት።