በኢራን ፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለችው ግለሰብ መሞቷ ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Mahsa Amini Family
በኢራን የሞራል ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ህይወቷ ያለፈው ግለሰብ የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ።
የ22 ዓመቷ ማህሳ አሚኒ በቴህራን ፖሊስ መኪና ውስጥ ድብደባ እንደተፈጸመባት የዓይን እማኞች ከገለጹ ከቀናት በኋላም ነው መሞቷ የተነገረው። ይህንን ክስ ፖሊስ ውድቅ አድርጎታል።
በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙ አንዳንድ ሴቶች ሂጃብ ለመልበስ መገደዳቸውን በመቃወም ሂጃባቸውን አውልቀዋል ተብሏል።
ሃዘንተኞች "ሞት ለአምባገነኑ" የሚሉ መፈክሮች ያሰሙ ሲሆን ፖሊስም በምላሹም በህዝቡ ላይ ሲተኩስ የሚያሳይ ቪዲዮ ወጥቷል።
የማህሳ የቀብር ሥነ ሥርዓት የተፈፀመው በምእራብ ኩርዲስታን ግዛት በምትገኘው የትውልድ ስፍራዋ ሳቄዝ ነው።
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት የኢራን የጸጥታ ሃይሎች ተቃውሞውን ለማስቀረት በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ነበር።
አንዳንድ የተቆጡ ተቃዋሚዎች ወደ አካባቢው አስተዳዳሪ ጽህፈት ቤት መሄዳቸውን ዘገባዎች ጠቁመዋል።
የቢቢሲ ፋርስ አገልግሎት የደረሰው እና ያረጋገጣቸው ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት የጸጥታ ሃይሎች በተቃዋሚዎች ላይ ተኩስ ከፍተዋል።
በተጨማሪም የአካል ጉዳት እና እስር መኖሩ ተነግሯል። በትዊተር ላይ የወጡ ቪዲያዎች እንደሚያሳዩት የጸጥታ ኃይሎች የአስተዳዳሪው ጽህፈት ቤት ሲጠብቁ እና ወደ ህንጻው ለመቅረብ የሚሞክሩ ተቃዋሚዎችን በቁጥጥር ስር አውለዋል።
የማህሳ መቃብር ላይ “አልሞትሽም፣ ስምሽ ከሞቱት በላይ ነው” የሚል ጽሁፍም እንደሰፈረበት በማህበራዊ ሚዲያ ተጋርቷል።
ማህሳ ሂጃብ ባለመጠምጠሟ የተጣለውን ጥብቅ የአለባበስ መመሪያ ባለማክበር ማክሰኞ እለት በሞራል (ስነ ምግባር) ፖሊስ በቁጥጥር ስር ዋለች።
የዓይን እማኞች እንደገለጹት ከሆነ በፖሊስ መኪና ውስጥ እያለች ድብደባ እንደተፈጸመባት እና በኋላም ፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ገብታለች።
የኢራን ፖሊስ በበኩሉ ማህሳ “ድንገተኛ የልብ ድካም አጋጥሟት” ነው ሆስፒታል የገባችው በማለት ክሱን አስተባብሏል።
የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ በማህሳ የአሟሟት ምክንያት ላይ ምርመራ እንዲጀምር የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠይቀዋል።
በሰሜን ቴህራን የሚገኘው የካሳራ ሆስፒታል ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ማህሳ ሆስፒታል ስትገባ “በሞትና በህይወት መካከል እንደነበረች ነው”።
በኋላም አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የሆስፒታሉ ሰራተኞችን “የፀረ-መንግስት ወኪሎች” በማለት ከከሰሱ በኋላ መግለጫው ከሆስፒታሉ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ እንዲወገድ ተደርጓል።












