ታዋቂ ሰዎች የህጻናት የዱቄት ወተትን ማስተዋወቃቸው ለምን አሳሳቢ ሆነ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እናት ኖት እንበል። ማኅበራዊ ሚድያን እየቃኙ ነው። ልጄን ማጥባት ላቁም ወይስ ምን ይሻላል? የሚል ሐሳብ ይዞዎታል።
ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ስለልጆች ምክር የሚለግስ ‘ግሩፕ’ ይቀላቀላሉ።
ሳያስቡት ማኅበራዊ ሚድያዎ የጨቅላ ሕፃናት የዱቄት ወተትን (ፎርሙላ ወተት) በሚያስተዋውቁ መልዕክቶች ይሞላል።
የዓለም ጤና ድርጅት ይህ ጉዳይ አሳስቦኛል እያለ ነው።
የድርጀቱ አዲሱ ዘመቻ ይህን “በዝባዥ” የሆነ “የጡት ወተት ምትክ” ገበያ ማስታወቂያን መግታት ነው።
የጡት ወተት ምትክ ፎርሙላ ወተት ተብሎ ይጠራል። ዝናውም በዓለም ናኝቷል።
የዓለም ጤና ድርጅት ሕፃናት ስድስት ወር እስኪሞላቸው ድረስ የእናታቸውን ጡት ወተት እየጠቡ እንዲያድጉ፤ መንግሥታትም ይህ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ይመክራል።
ከ6 ወራት በኋላ ግን የላም አሊያም የፍየል እንዲሁም ሌሎች ወተቶች ይመከራሉ።
ድርጅቱ ከ40 ዓመታት በላይ የእናት ጡት ወተት ጠቃሚ መሆኑን ሲመክር ቆይቷል። አሁን ባለንበት ዘመን የእናት ጡት ወተት የማጥባት ዝንባሌ በአሃዝ ሲሰላ 44 በመቶ ነው።
በአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ በተለይ አዳጊ በሚባሉ አገራት ፎርሙላ ወተት ጠጥተው ያደጉ ሕፃናት እየተጎዱ መሆኑን ተከትሎ ነበር ድርጅቱ በ1981 መመሪያ ያወጣው።
በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ማስታወቂያ ማስነገር የሚከለከልባቸው ከ6 ወር በታች ለሆናቸው ሕፃናት የሚሰጥ የፎርሙላ ወተት እና ትምባሆ ብቻ ናቸው።
ቢሆንም 32 አገራት ብቻ ይህን ሕግ ተግባራዊ ማድረጋቸው ድርጅቱን አሳስቦታል።
የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ጄኔቫ ላይ ለቀናት ተገናኝቶ በበይነ-መረብ የሚሰራጩ ማስታወቂያዎችን እንዴት መግታት እንችላለን ሲል መክሯል።
ነገር ግን የፎርሙላ ወተት ኢንዱስትሪ በየዓመቱ 55 ቢሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀስበት ነው።
ይህ ማለት የዓለም ጤና ድርጅት ከባድ ሥራ ከፊቱ ይጠብቀዋል ማለት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“ልጄ በቂ ወተት አያገኝም”
ስሟ ለዚህ ፅሑፍ ሲባል የተቀየረው ቲፕ ታይላንዳዊት እናት ናት።
እሷ እንደምትለው ማኅበራዊ ሚድያን ለመጎብኘት በገባች ቁጥር ተፅዕኖ ፈጣሪዎች፣ ታዋቂ የቴሌቪዥን ሰዎች ፎርሙላ ወተት ሲያስተዋውቁ ታያለች።
ልጇ ሆስፒታል ውስጥ ከተወለደ ጊዜ ጀምሮ ፎርሙላ ወተት እየሰጠችው እንዳደገች ቲፕ ትናገራለች።
ለልጄ የሚሆን በቂ ወተት አላመነጭም ብላ ብትሰጋም ይህ ግን እውነት አይደለም።
ልጇ አሁን ሦስት ወሩ ነው። በወር 50 ዶላር እያወጣች አሁንም ፎርሙላ ወተት መግዛቷን ቀጥላለች።
“ተመሳሳይ ‘ብራንድ’ የምጠቀመው ሆስፒታሉ ለልጄ ስለሰጠው ነው። ልጄ ወተቱን ሲጠቀም ምንም ዓይነት አለርጂ ወይም ችግር አላጋጠመውም።”
ልጇን ጡት አጥብታ ፎርሙላ ወተት የምትጨምርለት ቲፕ “ልጄ በቂ ወተት አያገኝም ብዬ እጨነቃለሁ። ለዚያ ነው ሁለቱንም የምሰጠው” ትላለች።
ታይላንዳዊቷ እናት ለቢቢሲ እንደተናገረችው ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የምታያቸው ማስታወቂያዎች ውሳኔዎቿ ላይ ተፅዕኖ እያሳደሩ እንደሆነ ይሰማታል።
“ገጼ ላይ የማያቸው ማስታወቂያዎችን ሸምድቸዋለሁ። ልጄ ለጨቅላ ሕፃናት ከሚሰጥ ወተት አደግ ሲል ምን ላድርግ የሚለው ውሳኔዬ ላይ ተፅዕኖ እንዳሰደሩብኝ ይሰማኛል።”
ኃላፊነቱ የማን ነው?
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ፎርሙላ ወተት የሚያመርቱ ድርጅቶች ከዚህ ቀደም ከምናውቀው ለየት ያለ የማስታወቂያ መላ እየተጠቀሙ ነው።
የማኅበራዊ ሚድያ መልዕክቶች፣ የቀጥታ ሥርጭቶች፣ ጌም፣ ፖድካስት፣ ዳርክ ፖስት፣ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እና ስለሕፃናት የሚያወሩ ቡድኖችን እየተጠቀሙ ነው።
ዳርክ ፖስት ማለት ኩባንያው ዒላማ ያደረጋቸው ሰዎችን የሚደርስበት፣ ነገር ግን የኩባንያው ገጽ ላይ የማይገኙ መልዕክቶች ማለት ናቸው።
መቀመጫውን ጄኔቭ ያደረገው የዓለም ጤና ድርጅት መሰል ማስታወቂያዎችን ለመግታት የሚያስችለውን መመሪያ ባለፈው ኅዳር ይፋ አድርጓል።
ድርጅቱ፤ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ “ምትክ ወተት” የሚያስተዋውቁ እና የሚተባበሩ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል ይላል።
መንግሥታት ደግሞ መሰል ማስታወቂያዎችን እንዲቆጣጠሩ አሊያም ለተጠቃሚዎች እንዳይደርሱ ሊያደርጉ፤ አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ሊያስወግዱ ይገባል ሲልም ይመክራል።
ምንም እንኳ አንዳንድ አገራት መመሪያው ጠንከር ሊል ይገባል የሚል ሐሳብ ቢያቀርቡም፣ አስገዳጅ ሕግ የመወጣቱ ዕድል ጠባብ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
‘የሕፃናት ወተት’
የጤና ድርጅቱ የሚመክረው ጨቅላ ሕፃናት ስድስት ወር ካለፋቸው በኋላ ምግብ መመገብ እንዲጀምሩ ነው። ነገር ግን ሁለት ዓመት እስኪሆናቸው ድረስ የእናት ጡት ወተትን ማጥባት ይመክራል።
ነገር ግን በርካታ እናቶችን ዒላማ የሚያደርጉ ማስታወቂያዎች “የሕፃናት ወተት” እንዲሰጧቸው ይመክራሉ።
ባለፈው ኅዳር አንድ ጥናት ያወጣው የአሜሪካ የፔዲያትሪክስ አካደሚ 12 ወር ላለፋቸው ሕፃናት የሚሰጡ ወተቶች ምንም ዓይነት የተለየ ጥቅም የላቸውም።
አካደሚው እንደሚለው እናቶች “የተሻለ የአዕምሮ ዕድገት” አሊያም “የተሻለ በሽታን የመቋቋም አቅም” የሚል ማስታወቂያ ሲመለከቱ ጠንቀቅ ሊሉ ይገባል።
የአሜሪካ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ማዕከል ፎርሙላ ወተትን እንደሚቆጣጠረው የሕፃናት ወተት ተብለው የሚሸጡ ወተቶችን አይቆጣጠርም።
የፔዲያትሪክስ አካደሚው የሕፃናት ወተት ተብለው የሚሸጡት ምርቶች ሱቆች ውስጥ ከፎርሙላ ወተቶች አጠገብ መቀመጥ የለባቸውም፤ ምክንያቱም ለእናቶች ግርታን ስለሚፈጥሩ ሲል ይከራከራል።
የማስታወቂያ ዘዴዎች
ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ላንሴት የተሰኘቸው የብሪታኒያ የሕክምና መፅሔት ፎርሙላ ወተት የሚሸጡ ድርጅቶች የሚጠቀሙትን የማስታወቂያ ዘዴ የሚተች ዕትም አስነብቧል።
ሪፖርቱ እንደሚያትተው እኒህ ድርጅቶች ፎርሙላ ወተቶች “ለአዕምሮ ዕደገት ጠቃሚ ናቸው” እያሉ ማስተዋወቃቸው ተገቢ አይደለም።
ጽሑፉን ካሳተሙት መካከል የሆኑት የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ተባባሪ ፕሮፌሰሯ ዶክተር ሲሲላ ቶሞሪ፤ ቤተሰብ እኒህ ወተቶች ተጨማሪ ንጥረ ነገር አላቸው ብሎ ያምናል ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
የጡት ማጥባት ሳይንስ ባለሙያ የሆኑት ዶክተሯ ሳይንሳዊ ቃላትን ለማስታወቂያ መጠቀም ትክክል አይደለም ይላሉ።
“ልጆቹ በጣም ብልህ እንደሆኑ የሚጠቁሙ ማስታወቂያዎች ይጠቀማሉ። አንዳንዶቹ ቃላት ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ ፎቶ ይጠቀማሉ” ይላሉ ዶክተሯ።
አልፎም ሕፃናት “እንዳይነጫነጩ፣ እንዳያለቅሱ” እና የመሳሰሉ ጥቅሞች አላቸው ብለው እንደሚያስተዋውቁ የታዘቡት ሲሲላ “ይህ የተለመደ የሕፃናት ባሕሪ ሊሆን ይችላል” ይላሉ።
አፕታሚል የተባለውን ወተት የሚያመርተው ዳኖን የተሰኘው ኩባንያ ለ50 ዓመታት ያህል ፎርሙላ ወተትን የተመለከተ ጥናት ሠርተናል ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።
“ሳይንሳዊ የሆኑ በክሊኒካል ጥናት የተደገፉ ፎርሙላዎች” የድርጅቱ የማስታወቂያ መርሆ ነው።












