ጋሪ ሊኒከር እና አለን ሽረር የቢቢሲ ቀዳሚ ከፍተኛ ተከፋዮች ሆኑ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞ የእግር ኳስ ተጫዋች እና የአሁኑ የስፖርት ተንታኝ ጋሪ ሊንከር ለስድስት ተከታታይ ዓመታት የቢቢሲ ከፍተኛው ተከፋይ ሆነ።
የቢቢሲ የስፖርት ፕሮግራም የሆነው ‘ማች ኦፍ ዘ ዴይ’ ፕሮግራም አቅራቢው ሊኒከር፣ በዓመት 1.35 ሚሊዮን ፓወንድ (በወር 7.6 ሚሊዮን ብር) ተከፋይ በመሆን ቁጥር አንድ የቢቢሲ ተከፋይ ሆኗል።
በማች ኦፍ ዘ ዴይ ፕሮግራም ላይ በቋሚነት በመቅረብ ትንታኔ የሚሰጠው አለን ሽረር ደግሞ በዓመት 445 ሺህ ፓዎንድ እየተከፈለው ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የቢቢሲ ሬዲዮ 2 ጋዜጠኛዋ ዞይ ቦል 980 ሺህ ፓወንድ ዓመታዊ ደሞዝ በማግኘት በግዙፉ ኮርፖሬሽን ውስጥ ሁለተኛ ደረጃ ተከፋይ መሆኗን የቢቢሲ ዓመታዊ ሪፖርት አሳይቷል።
በወር 112 ሺህ ፓወንድ የሚከፈለው ሊኒከር ከጥቂት ወራት በፊት ከስደተኞች ጋር በተያያዘ በሚሰጣቸው ፖለቲካዊ ይዘት ባላቸው አስተያየቶች ምክንያት ‘ገለልተኛ አይደለም’ በሚል ከሥራው ታግዶ ነበር።
የስደተኞች መብት ተቋርቋሪ የሆነው ጋሪ ሊኒከር የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የስደተኞች ፖሊሲን አጥብቆ በመተቸት ይታወቃል።
ሊኒከር ከሥራው እራሱን እንዲያገል በቢቢሲ ጥያቄ ከቀረበለት በኋላ ጉዳዩ የበርካቶች መነጋገሪ ከመሆኑም በላይ፣ የቢቢሲ የስፖርት ፕሮግራም አዘጋጆች እና ተንታኞች ለጋሪ ሊኒከር ድጋፋቸውን ለመግለጽ ከቢቢሲ ሥራዎች እራሳቸውን አግልለው ነበር።
በመጨረሻም ሊኒከር ከቢቢሲ ዋና ዳይሬክተር ቲም ዴቪ ጋር ውይይት ካደረገ በኋላ ወደ ሥራ ገበታው ተመልሷል።
በኮርፖሬሽኑ ውስጥ ቀዳሚ 10 ከፍተኛ ተከፋዮች መካከል አራቱ ሴቶች ናቸው። የቢቢሲ ዜና አንባቢዋ ሶፊ ራዎርዝ 365 ሺህ ፓወንድ ዓመታዊ ገቢ በማግኘት 10ኛ ደረጃን ይዛለች።
የ6ሙዚክ እና ዴዘርት አይላንድስ ዲስክስ አቅራቢዋ ሎረን ላቭረን 390 ሺህ በማግኘት 9ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ፊዮና ብሩስ ደግሞ 6ኛ ትልቅ ገንዘብ የምታገኝ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ሆናለች።

ከቀዳሚዎቹ 10 ጋዜጠኞች ውጪ ካለፈው ዓመት አንጻር ከፍተኛ የደሞዝ ጭማሪ ካገኙት መካከል ቀዳሚው በዎርልድ ሰርቪስ ቴሌቪዥን አውትሳይድ ሶርስ በተሰኘው ፕሮግራም የሚታወቀም ሮዝ አትኪንስ ነው።
የቢቢሲ ሬዲየ 4 ዘ ሚዲያ ሾው አቅራቢ እና የኮርፖሬሽኑ የትንተናዎች አርታኢ የሆነው ሮዝ አትኪንስ ዓመታዊ ደሞዙ 240 ሺህ ፓወንድ ደርሷል።












